የብልፅግና ፓርቲ ብሔር ብሔረሰቦችን ለአንድ አላማ በአንድነት የሚያሳትፍ ነው-------የዋግ ህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የብልፅግና ፓርቲ ብሔር ብሔረሰቦችን ለአንድ አላማ በአንድነት የሚያሳትፍ ነው-------የዋግ ህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አመራሮች
ኢዜአ ታህሳስ 4 ቀን 2012 ዓ.ም---የብልፅግና ፓርቲ ሁሉም የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ለአንድ ዓላማ በእኩል የማሳተፍ ዕድል ይፈጥራል ሲሉ በአማራ ክልል የዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አመራሮች ገለጹ።፡፡ የወላይታ ዞን አስተዳደር አመራሮች በበኩላቸው ፓርቲው የያዛቸው አካታች ዕሳቤዎች እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ለመተግበር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። በዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኙ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራም፣ ህገ ደንብ፣ አተገባበርና አስፈላጊነቱ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡ በውይይት መድረኩ ከተሳተፉት አመራሮች መካከል በዝቋላ ወረዳ የእንስሳት ሃብት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ቸኮለ እንዳሉት ኢህአዴግ ከግንባርነት ወጥቶ የአጋር ድርጅቶችን ያሳተፈ አዲስ ውህድ ፓርቲ መመስረቱ ህሉም ብሔር ብሄረሰቦች በአገሪቱ ጉዳይ ላይ እኩል ለመወሰን ያስችላቸዋል፡፡ ‘ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በላይ በአገሪቱ ፍትሃዊ የመሰረተ ልማት ስርጭት ባለመከናወኑ ምክንያት የብሔረሰብ አስተዳደሩ በልማት ወደ ኋላ መቅረቱን ተናግረዋል። አዲስ የተመሰረተው የብልፅግና ፓርቲ በአገሪቱ የእኩል መብት እና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በፕሮግራሙ ውስጥ ማካተቱ የዞኑን ህብረተሰብ የልማት ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል የሚል ተስፋ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡ በሰቆጣ ከተማ የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዘርፌ መረሳ በበኩላቸው እንዳሉት የብልፅግና ፓርቲ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ለአንድ ዓላማ በአንድነት እንዲቆሙ የሚያስችል ነው። "ብልፅግና ፓርቲ አርስ በርስ ከመገፋፋት እና ከመነቋቋር ፖለቲካ ወጥተን በአንድነት ለአገሪቱ ብልፅግና የበኩላችንን የምናበረክትበት ስርአት መፍጠር የሚያስችል ነው " ብለዋል፡፡ "የብልጽግና ፓርቲ ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝምን በትክክል ለመተግበር የቆመ ፓርቲ ነው" ያሉት ደግሞ የውይይት መድረኩን የመሩት የቀድሞው አዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የክልሉ የዲያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኃይሉ ግርማይ ናቸው። አመራሩ በውህደቱና በፓርቲው ፕሮግራምና አሰራር ላይ በቂ ግንዛቤ ይዞ ለታችኛው አባል ማስረፅ የሚችልበትን ስርዓት ለመዘርጋት በማሰብ መድረኩ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል። አመራሩ አዲስ በተዋሃደው ብልፅግና ፓርቲ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ይዞ ለአባላቱ ማስረፅ በሚችሉበት አግባብ ግልፅ የሆነ ውይይት እንደተካሄደ የተናገሩት ደግሞ የብሄረሰብ አስተዳደሩ የአዴፓ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽታው አዳነ ናቸው፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የመድረኩ ተሳታፊዎች በውህደቱ እና በፓርቲው ፕሮግራም እና ህገ ደንብ ላይ ያላቸውን ጥያቄ አንስተው በቂ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ አዲስ የተመሰረተውን የብልፅግና ፓርቲ አስፈላጊነት፣ በህገ ደንብ እና በፕሮግራሙ ላይ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ የሚካሄዱ መድረኮች እስከ ታህሳስ 15 ድረስ እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል። በውይይት መደረኩ ላይ ከ350 በላይ የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች መሳተፋቸው ታውቋል። በተመሳሳይ ዜና የብልጽግና ፓርቲ የያዛቸው አካታች ዕሳቤዎች እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ለመተግበር ፋይዳው የጎላ መሆኑን የወላይታ ዞን አስተዳደር አመራሮች ተናግረዋል። የወላይታ ዞን አስተዳደር አመራሮች በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና መሠረታዊ እሳቤዎች፣ በፓርቲው ህገ-ደንብና ቀጣይ የትግል አቅጣጫዎች ላይ ተወያይተዋል። በመድረኩ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ብልጽግና ፓርቲ በፕሮግራሙ ጠንካራና ተቀባይነት ያለው ዘላቂ መንግስታዊ መዋቅርና ተቋማት መገንባት ግብ እንዳለው ገልጸዋል። የብሔር ማንነት፣ የህዝቦች ዘላቂ ጥቅም ማስጠበቅና አገራዊ አንድነት ማጠናከር ግቡ እንደሆነ አስረድተዋል። "ብልጽግና ፓርቲ አሳታፊና አቃፊ ነው" ያሉት ዶክተር ጌታሁን፣ ሁሉም ዜጋ በኩራትና በሠላም የሚኖርባት አንድ ጠንካራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ዓላማ እንዳለው አስረድተዋል። የወላይታ ዞን አስተዳደር አቶ ዳጋቶ ኩምቤ በበኩላቸው ውህድ ፓርቲው ከዚህ ቀደም በአገራቸው ዕጣ ፈንታ በቀጥታ የመወሰን እድል የተነፈጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደባለቤትነት እንደሚያመጣ ተናግረዋል። "እውነተኛ የፌደራሊዝም ሥርዓት እውን በማድረግ የህዝቦች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የፓርቲው መነሻ ዕሳቤ ነው" ብለዋል። የፓርቲዎች መዋሀድ መሠረታዊ ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ አድርጓል ያሉት ደግሞ የዞኑ ዴሞክራሲ ተቋማት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ዮሐንስ ናቸው። የውይይት መድረኩ ዓላማ በየደረጃው ላሉ አመራርና አባላት የፓርቲ ውህደት ሥራ ያለበት ደረጃ ላይ የተደራጀና ግልጽ የሆነ መረጃ እንዲኖር ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። "ውህደቱ ባለፉት ዓመታት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች የተመዘገቡ ለውጦችን ጠብቆ ለማስፋት የሚያስችልና ስሕተቶችን በማረም የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት በዘላቂነት ለማሟላት ያለመ" ነው። በኢህአዴግ ውህደት ላይ የተደረገው ጥናት ወደ ተግባር እንዲገባ የሀዋሳው 11ኛው ደርጅታዊ ጉባኤ ያሳለፈውን ታሪካዊ ውሳኔ መነሻ በማድረግ ብልጽግና ፓርቲ መቋቋሙንም አመልክተዋል።