የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ዘመኑ በሚጠይቀው የለውጥ እንቅስቃሴ መቃኘት እንዳለባቸው ተገለፀ

9
የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ዘመኑ በሚጠይቀው የለውጥ እንቅስቃሴ በመቃኘት የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ በአግባቡ ሊያሳዩ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አሳሰበ። ጽህፈት ቤቱ በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው የስልጠና መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በዚህ ወቅት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፋ እንዳስታወቁት የኮሙዩኒኬሽን ሥራ ከዘመኑ ጋር እየዘመነ፣ የወቅቱን የተግባቦት መንፈስ እያጠና መጓዝን ይጠይቃል። ከዚህ ረገድ በየደረጃው የሚገኙ ኮሙኒኬሽንመዋቅሮች ኮሙኒኬሽን  ስራዎችን ለማሳለጥ የሚያደርጉት ጥረት ዓለም ከሚፈልገው የመረጃ ጥራት አንፃር ሲመዘን ብዙ ይቀረናል። በዚህም ምክንያት በየዘርፉ የተሰሩ ስራዎችና የተመዘገቡ ድሎች እንዲሁም የህዝቡ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች በተገቢው የኮሙዩኒኬሽን ስራ እንዳይታገዙ አድርጓል። በአሁኑ ወቅት ይህን ችግር ለማስተካከልና ሀገሪቱ የጀመረችው ሁለንተናዊ የለውጥ ግስጋሴ እውን እንዲሆን መንግስት ለኮሙኒኬሽን ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል። ዘርፉ የተጣለበትን ኃላፊነት በስኬት ወደታለመለት ግብ ማድረስ ይቻል ዘንድ ኮሙኒኬሽን ስራው ዘመናዊ፣ ፈጣንና ተደራሽ አቅጣጫ ተከትሎ ሊዘወተር እንደሚገባ አሳስበዋል። በዓለም ላይ የኮሙኒኬሽን ስራን ስኬታማ በሆነ መንገድ በመጠቀማቸው ሊታመኑ የማይችሉ የማህበረሰብ ለውጥና ሀገራዊ ህዳሴ እድገትን ማሳየት መቻላቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ለአብነት አንስተዋል። ከዚህ አኳያ ያሉን ከፍተቶችን በቀጣይ በማረምና ልምድ በመቀመር ዘመኑ በሚጠይቀው የግብዓት፣ ክህሎትና ተሰጥኦ በመታገዝ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ካሳሁን አሳስበዋል። የስልጠና መድረኩም የተዘጋጀው የሀገሪቱን የኮሙኒኬሽን አቅጣጫ ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር ታልሞ መሆኑን አስታውቀዋል። ያሉትን መልካም አድሎች በመጠቀም የተግባቦት ሂደቶችን ፈጣን፣ ተደራሽ፣ አስተማማኝና ዘመናዊ ለማድረግ  ጭምር ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም