የኢትዮጵያ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ከአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር እየተወያየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ከአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር እየተወያየ ነው
ኢዜአ ታህሳስ 4 ቀን 2012 ዓ.ም--- የኢትዮጵያ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ከአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በኮሚሽኑ ዓላማዎች ላይ እየተወያየ መሆኑ ተገለጸ። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስና የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በትውውቅ መድረኩ ላይ እንዳሉት ኮሚሽኑ ለዘመናት የዘለቀውን የአገሪቱን ህዝቦች ትስስር ለማጠናከር ይሰራል። የኮሚሽኑ ዓላማ አንድነቷ የተጠበቀና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ያለፉ ቁርሾዎችን በእርቅ ምዕራፍ በመዝጋት መላውን ህዝብ በቀጣይ በጋራ ለማሰለፍ መሆኑንም ገለጸዋል። "ህዝቡ ከአባቶቹ የወረሰውን የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የመተሳሰብና ሌሎች እሴቶችን በማጎልበት አሁን የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ኮሚሽኑ ትኩረት ስጥቶ ይስራል" ብለዋል። በተለይ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን ሁከትና ብጥብጥ ለማስቆም በአገር ባህልና ወግ መሰረት እርቅ ማካሄድ ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑንም ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ተናግረዋል። እውነተኛ ሰላም የሚመጣው በተለያዩ ግለሰቦችም ሆነ በህዝቦችና ብሔር ብሔረሰቦች መካከል ከልብ የመነጨና እርቅ ሲካሄድ መሆኑን ጠቁመው፣ "ቅሬታ ባላቸው አካላት መካከል ትክክለኛ እርቅ እንዲኖር እንሰራለን" ሲሉ ገልጸዋል። የተሳካ እርቅ በመፈጸም ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈንም መላው የአገሪቱ ህዝቦች ለኮሚሽኑ ሙሉ ድጋፍ በማድረግ ከጎኑ እንዲሰለፉም ጠይቀዋል። የአማራ ክልል መስተዳደርና ህዝብም የኮሚሽኑን ዓላማ፣ ተግባርና የሚያስገኘውን ዘላቂ ጥቅም በመረዳት ለኮሚሽኑ ቀጣይ ሥራ ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል። በውይይት መድረኩ ላይ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በመሳተፍ ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።