ቀጥታ፡

የብሄር ብሄረሰቦች በዓላት ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚገኝባቸው ናቸው … ባለሙያዎች

ኢዜአ፤ ታህሳስ 4/2012 የብሄር ብሄረሰቦች በዓላት ለሙዚቃ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ግብዓት የሚገኝባቸው ናቸው ሲሉ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

በዓላቶቹ ካሏቸው የተለያዩ ጠቀሜታዎች መካከል ለሙዚቃ ኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ የብሄር የብሄረሰቦች  ዘፈኖች ጭፈራዎች እና የሙዚቃ መሳሪያዎች ይገኙበታል ነው ያሉት፡፡

በጌዴኦ ዘመናዊ ዘፋኝነቱ የሚታወቀው አርቲስት አክሊሉ ዮሀንስ /ጀባቲ/ በሰጠው አስተያየት በአሁኑ ወቅት በርካታ ወጣት ድምፃዊያን የብሄር ብሄረሰብ ዘፈኖችን በዘመናዊ መንገድ በማቅረብ ብሄረሰቦቹን እያስተዋወቁ ነው።

ባህላዊ እሴቶቹን በኪነጥበብ ስራ በዘመናዊ መንገድ ማቀናበር ለሀገር ውሥጥም ሆነ በአለማቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ያለው ጠቀመታ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁሞ፤  በቅርቡ በአፍሪካ መድረክ ተሸላሚ የሆነው ወጣት ድምፃዊ አብረሃም በላይነህ /ሸላይቱን/ ለአብነት ጠቅሷል።

በርካታ የጌዴኦ ባህላዊ ዘፈኖችን በዘመናዊ መሳሪያ በማቀናበር ጌዴኦን በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በአለም መድረክ ለማስተዋወቅ ጥረት ማድረጉን የሚናገረው አርቲስት አክሊሉ በዓሉ ትክክለኛውን ሙዚቃና ባህል ለማንጸባረቅ ለሙዚቃ ባለሙያዎች መልካም አጋጣሚ ነው ብሏል።

በብሄር ብሄረሰቦች በዓል ላይ የሚቀርቡትን አይነት ባህላዊ አውደርእዮች በየጊዜው ቢዘጋጁ ለሀገራችን ሙዚቃ እድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልም ነው የተናገረው።

ሌላው የኪነጥበብ በባለሙያ የየም ብሄረሰብን የባህል ቡድን መሪ የሆኑት አቶ መልካሙ አበበ በበኩላቸው ፤ ብሔርብሔረሰቦች አንድ ላይ ተሰባስበው ባህላቸውን ማንጸባረቃቸው በርካታ የጥበብ ሰዎች የተለያዩ ግብአቶን የሚያገኙበት አጋጣሚን ይፈጥራል ይላሉ።

በበዓሉ ላይ ብሄር ብሄረሰቦች ይዘዋቸው የሚቀርቡት የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች በዘርፉ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎች ግብዓት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

እንደዚህ አይነት ዝግጅቶች እያንዳንዱ ብሄረሰብ ያለውን የሙዚቃ መሳሪያ ከሌላው ብሄረሰብ ጋር በማነጻጸር እና ክፍተቱን በማሻሻል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም አቶ መልካሙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም