የጠቅላይ ሚኒስትሩን መርህ ለማስቀጠል የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

78
ኢዜአ  ታህሳስ 3 / 2012   የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ መርህን ለማስቀጠል የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች በበኩላቸው በሰላም የተገኘው ዓለም አቀፍ እውቅና በሌሎች ዘርፎችም እንዲደገም ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው ደስታ እንደተሰማቸውም ተናግረዋል። የሆሳዕና ከተማዋ ነዋሪዎች ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሸለም የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እንዳሉት ዶክተር አብይ ወደስልጣን በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስምና ተቀባይነት ከፍ ያደረገ ሥራ ሰርተዋል። ሥራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝቶ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸውም መደሰታቸውንም ነው የገለጹት። የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ በደስታ መግለጫ ሰልፉ ላይ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ ያገኙት ሽልማት ከሰሩት ሥራ አንጻር የሚገባቸው ነው። የፖለቲካ እስረኞችን በማስፈታት፣ ለብዙሀን መገናኛዎች በሰጡት ነጻነት፣ በጎረቤት አገራት ሰላም እዲሰፍን በሰሩትና ከኤርትራ ጋር ለተፈጠረው ሰላም ያበረከቱት አስተዋጽኦ ተሸላሚ እንዳደረጋቸው አስታውሰዋል፡፡ "የዞኑ ህዝብ የእሳቸውን አርአያነት በማስቀጠል የተጀመረውን የመደመር ጉዞ ለማስቀጠል ከጎናቸው ልንቆም ይገባል" ያሉት አቶ አሸናፊ፣ ህዝቡ ሰላምን በማረጋገጥ ለውጡን ከዳር እንዲያደርስ ጥሪ አቅርበዋል። በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተገኙት የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጸደቀ ላምቦሮ እንዳሉት የጠቅላይ ሚኒስተር ደክተር አብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆን ለሀገር ኩራትና ክብር ነው። በሽልማቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ህብረተሰቡ ከራሱ አልፎ የሌሎችን ሰላም በማስጠበቅ ለአገሩ ሰላም መጎልበት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል። "የጎረቤትን ሰላም መጠበቅ የራስን ሰላም መጠበቅ ነው" ያሉት ዶክተር ጸደቀ፣ በሚሰሩበት የትምህርት ተቋም ሰላማዊ እንቅስቃሴው እንዲኖር በማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላም ጉዞ ለማስቀጠል እንደሚሰሩ ገልጸዋል። "ዶክተር አብይ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንድታገኝ ማድረግ ካስቻላቸው አንዱ ለሰላም ያላቸው ተነሳሽነት ነው" ያሉት ደግሞ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ቀለመወርቅ ወልዱ ናቸው፡፡ የሰላም ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ የሰሯቸው ስራዎች እውቅና አግኝተው ለሽልማት በመብቃታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን መርህ አጠናክረው በማስቀጠል የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡ ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አበበች በየነ በበኩላቸው እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጎረቤት አገራት ሰላምን በማምጣት በኩል ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ "በጠቅላይ ሚኒስተሩ ሽልማት ደስተኛ ነኝ" ያሉት ወይዘሮ አበበች እናቶች ለአገር ሰላም መስፈን ድርሻቸው የጎላ በመሆኑ የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ ለአገራዊው የመደመርና የሰላም ጉዞ እገዛ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል በተመሳሳይ ዜና በሰላም የተገኘው ዓለም አቀፍ እውቅና በሌሎች ዘርፎችም እንዲደገም ጠንክረው እንደሚሰሩ የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች ገልጸዋል። የጌዴኦ ዞን ህዝብና አስተዳደር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የሰላም ኖቬል ተሸላሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። "ኮርተናል" በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀ መድረክ ላይ የአገር ሽመግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ተሳትፈዋል። የጌዴኦ ባህላዊ የባሌ አስተዳደር ስርዓት መሪ አባ ጋዳ ዳንቦቢ ማሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት የጠቅላይ ሚኒስተሩ ሽልማት የአገር ሽልማት ነው። "በሰላም የተገኘው ዓለም አቀፍ እውቅና በሌሎች ዘርፎች እንዲደገም ጠንክረን መሰራት ይኖርብናል" ሲሉም ተናግረዋል። በተለይ ወጣቶች አገር አፍራሽ ከሆኑ አጀንዳዎች እራሳቸውን በማራቅ አሁን የተገኝው ሰለም እንዲጠናከር የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። "የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት ለሁላችን የኩራት ምንጭ ነው" ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ ናቸው። በሽልማቱ የጌዴኦ ህዝብ ከፍ ያለ ደስታ እንደተሰማው ገልጸው ሽልማቱ አገሪቱን በመልካም ስም እንደሚያስጠቅስና  ለቀጣይ ስራ ስንቅ እንደሚሆን ተናግረዋል። በዞኑ የብልጽግና ፖርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፀሐይ ወራሳ በበኩላቸው "ሽልማቱ ዶክተር አብይ በቀጣይ ጠንክረው እንዲሰሩና አገሪቱን ወደ ከፍታ ማማ ለማሽጋገር የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል" ቢለዋል። በሰለም የተገኘው ዓለም አቀፍ እውቅና በሌሎች ዘርፎች እንዲደገም ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ሲሉ ኃላፊዋ ተናግረዋል። በመድረኩ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም