ቀጥታ፡

የአገሪቷ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው የእርሻ መሬት ከማስፋፋት ባለፈ ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል-ጥናት

አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 ግብርናው በአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ቀጣይነት እንዲኖረው የእርሻ መሬት ከማስፋፋት ባለፈ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ። በአገሪቷ ተጨባጭ እድገት እየተመዘገበ ቢሆንም በተለይም የግብርናው ዘርፍ የሰው ኃየል ቁጥርን እና የእርሻ መሬትን በማስፋት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ "የአቅጣጫ ለውጥ ካልተደረገ ቀጣይነቱ ያጠራጥራል" ተብሏል። የምጣኔ ሀብት መምህርና አማካሪ አቶ ኤርሚያስ ደመረ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የተመዘገበው እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው የአሰራር ለውጥ እንደሚያስፈልገው በጥናት ለይተዋል። "የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ትንተና" በሚል ርዕስ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ 1995 እስከ 2010 ባደረጉት ጥናት "የአገሪቷ የግብርና ምርት እድገት የተመዘገበው የእርሻ መሬትን በማስፋፋትና የሰው ጉልበት ቁጥር በማሳደግ ነው"። እንደ ጥናቱ በአገሪቷ በ1995 የነበረው 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት ወደ 11 ሚሊዮን ሄክታር በማደጉ የተገኘ የምርት ጭማሪ መሆኑን ገልጸዋል። በተመሳሳይ በግብርና ምርት ላይ የተሰማራው የሰው ኃይል ከ 40 እስከ 50 በመቶ ጭማሪ በመኖሩ በግብርና ምርቱ "ተፈጥሯዊ እድገት ያመዝናል" ብለዋል። የጥናቱ ውጤት የሚያመላክተው የኢኮኖሚ እድገቱ በአብዛኛው ምርታማነትን በማሳደግ የመጣ ሳይሆን የእርሻ መሬትና የሰው ኃይል መጠኑን መሰረት ያደረገ እንደሆነም ገልጸዋል። በመሆኑም በዘርፉ እቅድ ሲወጣም ጥቅም ላይ የዋለው የሰውና የመሬቱ ስፋት መጠን ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ ካበረከተው አስተዋጽኦ አንጻር መቃኘት አለበት ነው ያሉት። እንደ ተመራማሪው ገለጻ የእርሻ መሬቱ እና የሰው ኃይል መጠኑ ባለበት ሲቆም የግብርና ምርቱ እድገቱ እንዳይገታ "የግብርና ምርታማነት ላይ ማተኮር ይገባል" ብለዋል። በአገሪቷ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብም ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አንዲሁም አፈፃፀማቸውም ምርትና ምርታማነትን ከማሳደጉ ጋር መቃኘት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም