የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ለሚኖሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች የተሽከርካሪ ድጋፍ አደረገ

70

ኢዜአ ታህሳስ 3 ቀን 2012 ዓ.ም     የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ለሚኖሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መገልገያ የሚውል የተሽከርካሪና የአምቡላንስ ድጋፍ አደረገ። ለስደተኞቹ የተበረከቱትን አንድ አቡላንስና አንድ ተሽከርካሪ የጃፓን አምባሳደር  ለኢትዮጵያ የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስረክቧል።

በርክክቡ ወቅትም የጃፓን አምባሳደር ሚስተር ማትሱናጋ ዳይሱኬ ባደረጉት ንግግር፣ በአመቱ መጀመሪያ በጋምቤላ የሚገኙትን የስደተኞች ካምፕ መጎብኘታቸውን ገልዋል።

በወቅቱም የተሽከርካሪዎች ክፍተት መኖሩን በመገንዘብ በጋምቤላ ካምፕ ኩኛክ ማዕከል ለሚገኙት እናቶችና ሌሎች ስደተኞች ከካምፕ ወደ ህክምና ማዕከላት ለማመላለስ ይረዳ ዘንድ የተበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

የጃፓን መንግስት በቀጣይም በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አክለዋል።

በኢትዮጵያ የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ያላ በበኩላቸው እንዲህ ያለው አካባቢ ተኮር ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ የጃፓን መንግስት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች በሚኖሩባት ኢትዮጵያ በርካታ ድጋፍ የሚያስፈልግ በመሆኑ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሚኖሩት ስደተኞች ከ26 የአለም አገሮች የመጡ ሲሆን በ27 ካምፖች እርዳታና ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም