ኢትዮጵያ በዱባይ 2020 ኤክስፖ ስራዎቿን በምታስተዋውቅበት ስፍራ የድንኳን ግንባታ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዱባይ 2020 ኤክስፖ ስራዎቿን በምታስተዋውቅበት ስፍራ የድንኳን ግንባታ እየተካሄደ ነው
ኢዜአ 3/2012 ኢትዮጵያን ጨምሮ 192 አገሮች በሚሳተፉበት የዱባይ 2020 ኤክስፖ ኢትዮጵያ ስራዎቿን በምታስተዋውቅበት ስፍራ የድንኳን ግንባታ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ለዚሁ ዝግጅት ኢትዮጵያ ከዱባይ አስተዳደር የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አግኝታለች፡፡ ኢትዮጵያ በዱባይ 2020 ኤክስፖ ያላትን ተሳትፎ በይፋ ያሳወቀችበት ስነ-ስርዓት ትናንት ማምሻውን ተካሄዷል። "አዕምሮዎችን በማስተሳሰር ወደፊትን መፍጠር" በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የዱባይ 2020 ኤክስፖ ከጥቅምት እስከ መጋቢት 2013 ዓ.ም. ለስድስት ወራት ይካሄዳል። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋናው አርጋ ኢትዮጵያ በይፋ ኤክስፖ ላይ እንደምትሳተፍ ባበሰሩበት ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በኤክስፖው ላይ ለሚኖራት ተሳትፎ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወነ ነው። የኤክስፖው ተሳታፊ አገሮች የራሳቸው የሆነ ስራቸውን የሚያሳዩበት ድንኳን (ፓቪሊዮን) ግንባታ እየካሄዱ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዱባይ አስተዳደር የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የኢትዮጵያ የድንኳን ግንባታ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል። ግንባታው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተው፤ የዱባይ አስተዳደር ለድንኳን ግንባታ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ኤክስፖው ምርቶቿንና ስራዎቿን ማስተዋወቅ በምትችልበት ሁኔታ ላይ የቴክኒክ ድጋፎችን እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ በበኩሏ በኤክስፖ ላይ ለምታከናውናቸው ስራዎች በቂ ነው ባይባልም ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ የመነሻ በጀት መመደቧንም ነው አምባሳደር ምስጋናው የጠቆሙት። ኢትዮጵያ የተለያዩ እምቅ ታሪኮቿን እንዲሁም የንግድና ኢንቨስትመንት እምቅ አቅሟን ለዓለም ገበያ እንደምታስተዋውቅ ገልጸው፤ ''ምድረ ቀደምት የሚለውን የቱሪዝም መለያ በማስተዋወቅ ኢትዮጵያ የብዙ ነገሮች መነሻ መሆኗን የማሳየት ተግባር ይከናወናል'' ብለዋል። አገሪቷ በግብርና ማቀነባባሪያ፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳና በቆዳ ውጤቶች፣ በማዕድን፣ በኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂና ሌሎች መስኮች ያላትን እምቅ አቅም እንደምታስተውቅም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በዱባይ 2020 ኤክስፖ አስመልክቶ ስራዎችን በቅንጅት ለመምራት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣በባህልና ቱሪዝም ሚኒስተር፣የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ሌሎች ተቋማት አባል የሆኑበት ብሔራዊ የሴክሬተሪያት ቢሮ በነሐሴ 2011 ዓ.ም መቋቋሙንም አስታውሰዋል። የዱባይ የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማህበራት የዓለም አቀፍ ቢሮዎች ዳይሬክተር ኦማር ካን ኤክስፖው ኢትዮጵያ በንግድና ኢንዱስትሪ መስክ ያላትን እምቅ አቅም በማስተዋወቅ ትልቅ የገበያ እድል የምታገኝበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ''ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች በተጨማሪ የተለያዩ የሃይል አማራጮች ለንግድ ኢንቨስትመንት የተዘጋጁ ነጻ ቀጠናዎች አሏት'' ብለው፤ ኤክስፖውም የኢኮኖሚ አቅሟን ለማጎልበት እንደሚያግዛት አመልክተዋል። የተባበሩት ዓረም ኤምሬቶች ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት ከሚሰማሩባቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ዋነኛ የንግድ አጋር በመሆኗ የዱባይ የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማህበራት በአፍሪካ የመጀመያውን በዓለም ሁለተኛ ቢሮውን በኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2013 መክፈቱን አስታውሰዋል። ኢትዮጵያና የዱባይ አስተዳደር ነዳጅን ሳይጨምር አጠቃላይ ያላቸው የንግድ ልውውጥ መጠን 675 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ጠቅሰዋል። ''የዱባይ አስተዳደር የኢትዮጵያ ምርቶችና አገልግሎቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቁና ገበያ እንዲያገኙም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል'' ብለዋል። በኤክስፖው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም እንደሚዘጋጅም ጠቁመዋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የአፍሪካ አገሮችን የኤክስፖ ተሳትፎ በአስተባባሪነት እንደሚመራም ተመልክቷል። ኢትዮጵያ 25 ሚሊዮን ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ በሚጠበቀው የዱባይ 2020 ኤክስፖ የምታሳያቸውን ምርቶች፣ አገልግሎቶችና ትርኢቶች 750 ሺህ ሰዎች እንደሚጎበኙት ተገምቷል። ኢትዮጵያ በኤክስፖው 550 የቢዝነስ ለቢዝነስ ትስስሮችና 250 ጊዜ የሚዲያ ሽፋን ለማግኘት እቅድ ይዛለች። በተጨማሪም የ192 አገራቱ ብሔራዊ ቀናት በኤክስፖ ላይ የሚከበር ሲሆን የኢትዮጵያ ቀንም በመጋቢት 2013 ዓ.ም. የሚከበር ሲሆን የተለያዩ ባህላዊና ታሪካዊ ትርኢቶችን ታሳያለች ተብሏል። ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2015 በተካሄደው የሚላን 2015 ኤክስፖ የቡና ምርቷን በማስተዋወቅ ተሳትፎ ማድረጓ ይታወሳል። በየአምስት ዓመቱ አንዴ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ኤክስፖ እ.አ.አ በ2025 በጃፓን ኦሳካ ከተማ የሚካሄድ ይሆናል።