ያልተዘጉ የመንገድ ዳር ቱቦዎች ለጤና እና ለአካል ጉዳት አየዳረጉን ነው...የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ያልተዘጉ የመንገድ ዳር ቱቦዎች ለጤና እና ለአካል ጉዳት አየዳረጉን ነው...የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች
ኢዜአ፤ ታህሳስ 3/2012 በመቀሌ ከተማ ከፍሳሽ ውሃ መውረጃ ቱቦ የሚወጣ መጥፎ ጠረን ለጤና ችግር እያጋለጣቸው መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ክዳን የሌላቸውን ቱቦዎች ለመዝጋት 20 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ወደሥራ መገባቱን የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ የከተሞች ጽዳትና ውበት ኤጀንሲ አስታውቋል።
ነዋሪዎች የተከፈቱ ትቦዎች ፈጥነው ባለመከደናቸው ለአደጋ እየተጋለጡ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት በመቀሌ ዋና ዋና የአስፋልት መንገዶች ዳር ያሉ የቆሻሻ ውሃ ማፋሰሻ ቱቦዎች ክዳን የሌላቸውና አንዳንዶቹም ክዳናቸው የተሰበረ በመሆኑ በደረቅ ቆሻሻ እየተዘጉ ነው።
ይህም ከፈሳሽ ቆሻሻ በሚወጣ መጥፎ ጠረን ለጤና እክል እየዳረጋቸው ከመሆን ባለፈ ሰዎች በጉድጓድ ውስጥ እየገቡ ለተለያዩ የአካል ጉዳት እየተዳረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
“ለፍሳሽ ቆሻሻ ማስገቢያና ማስተንፈሻ በሚል የተዘጋጁት ፖሰቲዎች ክዳን የሌላቸውና አንዳንዶቹም በመሰባበራቸው ለጉዳት እየተዳረገን ነው” ያሉት ደግሞ በከተማው የሀውልት ክፍለከተማ ነዋሪ አቶ ዘርኡ አጽብሃ ናቸው።
በአካባቢያቸው ከ100 በላይ የፈሳሽ ቆሻሻ መውረጃ ፖሰቲዎች ክዳን ስለሌላቸው በተለያዩ ደረቅ ቆሻሻዎች እየተሞሉና እየተዘጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በእዚህም ፍሳሽ ቆሻሻ መሄጃ አጥቶ በመጠራቀም መጥፎ ሽታ እየፈጠረና ለጤና ጠንቅ እየሆነባቸው መሆኑን አስረድተዋል።
በከተማው የዓዲ-ሐ ጤና ጣቢያ ባለሙያ ሲስተር ኪሮስ አማረ በበኩላቸው፣ “ፖሰቲዎች ፈጥነው አለመከደናቸው ተደፍነው ቆሻሻ ውሃ በማቆር ለተለያዩ በሽታዎች ምንጭ እየሆኑ ነው" ብለዋል።
ከጤና ችግር ባለፈ አቅመ ደካሞችና ህጻናት ክዳን በሌለው ፖሰቲ ውስጥ በመግባት ለአካል ጉዳት የተዳረጉበት ሁኔታ መኖሩንም አስረድተዋል።
''በከተማው ውስጥ ከተዘጋጁ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስተንፈሻ ፖሰቲዎች አብዛኞቹ ክዳናቸው ሙሉ በሙሉ በመፈራረሱ የአደጋ ስጋት ሆነዋል” ያሉት ደግሞ በመቀሌ የቀዳማይ ወያነ ክፍለ ከተማ የሚኖሩት መምህር ሐሰን መሀመድ ናቸው።
የሚመለከታቸው አካላት እያዩ እንዳላዩ ዝም ማለታቸውን ጠቁመው፣ “አስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጠ ለጤና ጠንቅና ለአደጋ ስጋት መሆናቸው ይቀጥላል” ብለዋል።
በቱሪስት አስጎብኝነት የሥራ ዘርፍ የተሰማራው ወጣት ትካቦ ፀሃየ በበኩሉ፣ በከተማው ውስጥ የሚስተዋለው ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም እንቅፋት እየሆነ በመምጣቱ አፋጠኝ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቋል።
የሽታ አልባ ፍሳሽ መውረጃ ባለሙያ ወጣት አሰፋ ደርበው በበኩሉ፣ በከተማው ከ10 ሺህ በላይ ፖሰቲዎች በተለያዩ ደረቅ ቆሻሻዎች መዘጋጀታቸውን በጥናት መረጋገጡን ተናግሯል።
ደረቅ ቆሻሻን በማስቀረት ፍሳሽ ቆሻሻን ብቻ የሚያስወግድ ሽታ አልባ ትቦ በመስራት ችግሩን መከላከል እንደሚቻል አመልክቷል።
በትግራይ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ የከተሞች ጽዳትና ውበት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አዳነ ገብረፃድቅ እንዳሉት፣ የህብረተሰቡ ቅሬታ ትክክል መሆኑንና እንደሚጋሩት ተናግረዋል።
በተለያዩ የከተማው አካባቢዎች በማስተንፈሻ ፖሰቲዎች ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በ20 ሚሊዮን ብር አዳዲስ ክዳኖችና መሰል ስራዎችን የመስራት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
የከተማው ነዋሪዎችም የፈሳሽ ትቦ መውረጃዎችን ለፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ብቻ እንዲጠቀምባቸው ግንዛቤያቸውን የማሳደግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።