በባህር ዳር ከተማና አካባቢው የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀንን በፖናል ውይይት አከበሩ - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማና አካባቢው የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀንን በፖናል ውይይት አከበሩ
ኢዜአ ታህሳስ 3/2012 የፌዴራል ፖሊስ አባላት እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከኤች. አይ. ቪ/ኤድስ በመጠበቅ የሀገር ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። በባህር ዳር ከተማና አካባቢው የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የዓለም የኤች.አይ. ቪ. /ኤድስ ቀንን ትናንት በፓናል ውይይት አክብረዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተቀናጀ የኤች. አይ .ቪ/ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮግራም ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰብለ ትኩ ባቀረቡት የመነሻ ጽሁፍ እንደገለጹት የፌዴራል ፖሊስ አባላት የሀገራቸውን ሰላም ለማስጠበቅ እንደሚተጉት ሁሉ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከኤች አይ ቪ/ ኤድስ በሽታ በመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
በኢትዮጵያ የአዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በጋምቤላና አማራ ክልሎች በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ እንደሚገኝ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ገልፀዋል፡፡
የአማራ ክልል የከተማና የገጠሩን ጨምሮ የኤች አይቪ/ ኤድስ ስርጭት አንድ ነጥብ ሁለት በመቶ ሲሆን የጋምቤላ ክልል ደግሞ አራት ነጥብ ስምንት በመቶ ላይ እንደሚገኝ በማሳያነት አቅርበዋል።
"ፖሊስ የህብረተሰቡ አንዱ አካል እስከሆነ ድረስ እሱንም የሚያካትት ነው" ያሉት ወይዘሮ ሰብለ የፌደራል ፖሊስ አባላት በስራቸው ሁሌም በተጠንቀቅ እንደሚቆሙ ሁሉ እራሳቸውን ከበሽታው በመጠበቅ ለሌሎች አርያ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በሽታውን ለመከላከልም የ "መ" ህጎችን ማለትም መታቀብ፣ መወሰን እና መጠቀምን የስራቸው አንድ አካል ሊያደርጓቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፌዴራል ፖሊስ ስራዊት በሚገኘበት አካባቢ ሁሉ የማማከርና የመመርመር አገልግሎት እየሰጠ ስለሆነ የፖሊስ አባላቱ መመርመርና እራሳቸውን ማወቅ እንዳለባቸውም አስረድተዋል።
በበለፈው ዓመት ከ4 ሺህ በላይ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተመርምረው ራሳቸውን እንዳወቁ ጠቁመው በሽታው የተገኘባቸው አካላትም ተገቢው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ አባላት እራሳቸውን ከኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ እንዲከላከሉ አማራጮች ሁሉ በየአካባቢያቸው እንደተዘረጉ የገለጹት ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ በሽታ መከላከል ክፍል ሃላፊ ኮማንደር አርያ ገብረ ዋህድ ናቸው።
ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከል የሚያስችሉ አማራጮችን መጠቀም አለመቻል እራስን እንደማታለል ይቆጠራል ያሉት ኮማንደር አርያ የፌዴራል የፖሊስ አባላት ራሳቸውን ከበሽታው በመጠበቅ ለሌሎች አርአያ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ሰሜን ፈጥኖ ደራሽ ባልደረባ የሆኑት ኮማንደር ይመር አደም በበኩላቸው ኮሚሽኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ የሚያከናውነው በየዓመቱ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን ሲከበር ብቻ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በየዓመቱ በዘመቻ መልክ የሚሰጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ውጤታማ እንደማይሆን ጠቅሰው የፖሊስ ስራዊቱ ኤች አይ ቪ /ኤድስን መከላከል የእለት ተለት ተግባሩ እንዲያደርገው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው በየወሩ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
"ማህበረሰብ የለውጥ አቅም ነው" በሚል መሪ ሃሳብ በተከሄደው የፓናል ውይይት ላይ የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ አመራሮችና የአማራ ክልል ተጋባዥ የፖሊስ አባላት ተሳትፈዋል።