ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ለዓለም ማሳወቋ እንዳኮራቸው በደብረ ማርቆስና ጎንደር ነዋሪዎች ገለጹ

ኢዜአ ታህሳስ 3/2012 የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ሽልማት ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ለዓለም ያሳወቀ አኩሪ ውጤት መሆኑን በደብረ ማርቆስና ጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

ከደብር ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ዮሐንስ ግርማ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላም ኖቤል ሽልማት መድረስ ለሀገሪቱ ሆነ ለህዝቡ ከፍተኛ ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪው እንዳሉት ዶክተር አብይ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍ  ባከናወኗቸው ተግባራት ያገኙት ሽልማት የሀገሪቱ ክብር ከፍ ያደረገና  ለሰላም ያላትን ቁርኝነት ያስመሰከረ ነው።

"ጠቅላይ ሚኒስተሩ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው ሀገሪቱ በቀጣይ ያላትን አቅም ተጠቅማ ለአካባቢውም ሆነ ለአለም ሰላም የምትሰራ መሆኑን መንግስታት እንዲገነዘቡ አድርጓል "ያሉት ደግሞ የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ሽመልስ እርገጤ ናቸው።

በዚህም ትኩረታቸውን ወደ ኢትዮጵያ በማድረግ ለልማት አጋዥ ኃይል እንዲሆኑ  የሚያስገድዳቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው ነዋሪ አቶ ዳዊት መሰለ የጠቅላይ ሚኒስተሩ የሰላም ኖቤል ሽልማት ሀገሪቱ ከታላላቅ ሀገራት ተርታ ስሟ እንዲነሳ ያደረገ በመሆኑ እንደሚያኮራቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ  ወዳጅ ሀገራትን በማፍራት በልማት መደጋገፍ የሚያስችላትን አቅም ለመፍጠር እንደሚያግዛትም ጠቁመዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎንደር ከተማ ነዋሪው አቶ እሸቱ ተረፈ እንደገለጹት ሽልማቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ኩራት ከመሆኑ ባሻገር ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚመሩት ፓርቲያቸው የአለም መንግስታት እምነት እንዲኖረው ያደርጋል።

በምስራቅ አፍሪካ የነበረውን ውጥረት በማርገብ  ወደ ሰላማዊ ግንኙነት መቀየራቸው ለሽልማቱ እንዳበቃቸው ሁሉ በሃገሪቱ አሁን እየታየ ያለውን ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ እንቅስቃሴና መፈናቀል ጊዜ ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው የሚጠቁም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የከተማ ነዋሪ አቶ ሳሙዔል ላቀቸው በበኩላቸው ሽልማቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሰላምና ለአንድነት እንዲሰራ ያነቃቃ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

"የሀገራችን ስምና ዝና በዛ የክብር መድረክ በሰፊው መነሳት ለኢትዮጵያ ኩራት ነው"  ብለዋል።

ሽልማቱ የመላ ህዝቡ በመሆኑ  ሀገሪቱ ወደ ነበረችበት  ከፍታ እንድትወጣ ሁሉም የድርሻውን ማድረግ እንዳለበት የሚያስገድድ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም