ቀጥታ፡

የጥምቀት ክብረ በዓል በዓለም አቀፍ ቅርስነት መመዝገቡ ለቱሪስት ፍሰቱ የጎላ ሚና አለው ተባለ

ኢዜአ ታህሳስ 2/2012 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ ክብረ በዓል ጥምቀት በዓለም በማይዳሰሱስ ቅርሶች መመዝገቡ ለቱሪስት ፍሰቱ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተገለጸ። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመሆን በዓሉን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሳይንስ፣ ትምህርትና ባህል ዩኔስኮ መመዝገብን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። የጥምቀት በዓልን በዓለም ከማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር እንዲካተት ለማድረግ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል። በዓሉ ከቅርሶች መስፈርት አኳያ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ምን ያህል ጠቃሚ ነው? የሚለው በጥናት ተለይቷል፤ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብም ሰነዶች ለዩኔስኮ መላኩን በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተጠቅሷል። በዚህም መሰረት የቅርሱ ስያሜ፣ምንነት፣የሚኖረው ጠቀሜታ፣በማን እንደሚተዳደርና የቅርሱን ዘላቂነት በሚመለከት የተዘጋጀው መጠይቅ ተሞልቶ ለዩኔስኮ ተልኳል። ከዚህ ባለፈም የበዓሉን ገጽታ የሚያሳይ የአስር ደቂቃ ቪዲዬ ለገምጋሚዎች እንዲደርስ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን የተመረጡ አስር ፎቶግራፎችም ታይተዋል። ዝርዝር መስፈርቱ ከታየ በኋላም በኮሎምብያ ዳጎታ በተካሄደው 14ኛው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ በይነመንግሥታት ኮሚቴ ጉባኤ ላይ በዓሉ በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት እንዲመዘገብ ተወስኗል። በዚህም በዓሉ ከገዳ፣መስቀልና ፍቼ ጨምበላላ ቀጥሎ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው አራተኛው ቅርስ መሆን ችሏል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ መሰረት ብዙነሽ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤የበዓሉ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኖቤል ሽልማት ጋር መገናኘቱ አገሪቷን ድርብ ድል ያገናጸፋት ነው። ''ጥምቀት ከኃይማኖታዊ በዓልነት የሚሻገር ወጣቶች አንድነት ህብረትና ፍቅራቸውን የሚገልጹበት ነው'' ያሉት ሚኒስትር ደኤታዋ አገሪቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ገጽታ ወደ ከፍታ የሚያሻገር ነው ብለዋል። ''ኢትዮጵያ ዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ አባል ሆና ተመርጣለች'' ያሉት ወይዘሮ መሰረት አገሪቷ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ እምቅ ቅርስ ባለቤት በመሆኗ ብዙ ማትረፍ የምትችልበት ዕድል መኖሩን አንስተዋል። በቀጣይም ሌሎች ቅርሶችን የማስመዝገቡ ሂደት በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ፍሰሃ በበኩላቸው፤ የጥምቀት ክብረ በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ለአገሪቷ የቱሪስም ፍሰት መጨመር የጎላ ሚና ይጫወታል። በዓሉ ወካይ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ዓለም አቀፍ ጥበቃ የሚያገኝበት መንገድ ለማመቻቸት እንደሚያስችል የገለጹት ዳይሬክተሩ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችን የሚስብ እንደሆንም አክለዋል። በዓሉ በተለይ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በጋራና በአንድነትን የሚያከብሩት በመሆኑ ይህንን ገጽታም የበለጠ ለማጠናከር እንደሚያግዝም ነው ያመለከቱት። የበደቡብ ፣ቤንሻንጉልና ጋምቤላ፣አማራ፣ትግራይ ሱማሌ፣አፋር፣ሀረሪ፣ሀዊ፣አርጎባ፣ዋግምራ፣ኩናማና ኢሮፕ ጨምሮ በአጠቃላይ 76 ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦችን የማይዳሰሱ ቅርሶች ምዝገባ በአገር አቀፍ ደረጃ መከናወኑን ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም