የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ በመመዝገቡ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ በመመዝገቡ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈች
ኢዜአ ታህሳስ 2/2012 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ በመመዝገቡ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈች። የጥምቀተ ክርስቶስ በዓል በኢትዮጵያ ስም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መግለጫ ተሰጥቷል። አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እንደገለጹት፤ በዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ መመዝገቡ ቤተ ክርስቲያኗ እና የኢትዮጵያ ህዝቦች ስም በዓለም ላይ ደምቆ እና ጐልቶ እንዲታወቅ ያደርጋል። እንደዚሁም አገሪቱን በቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትኾን ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ተብሎ እንደሚታመን ገልጸዋል። ''ሃይማኖታዊው፣ እጅግ ተወዳጁ እና ደማቁ የጥምቀት በዓላችን በዛሬው ዕለት የዓለም ቅርስ ኾኖ በዩኔስኮ ስለተመዘገበ እንኳን ደስ አላችኹ!'' ብለዋል። በየዓመቱ ጥር ዐሥራ አንድ ቀን የሚከበረው የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው በዓላት መካከል ጉልህ በዓል እንደሆነ ገልጸዋል። ''በመላ ሀገሪቱ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በኅብረት፣ በአንድነት፣ በሰላም፣ በስምምነት እና በፍቅር ታቦቱን አጅቦ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን እያመሰገነ በየወንዙ፣ በየዐደባባዩ እና በየመንገዱ በፍጹም ደስታ የሚያከብረው በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስ ነው'' ብለዋል። በዓሉ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ቤተ ክርስቲያኗ እና መንግሥት እንደዚሁም መላው ሕዝብ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሊቃውንት እና ዓበይተ ሀገር ምሁራን በአጠቃላይ ምእመናንና ምእመናት የማያቋርጥ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው አስታውሰዋል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የባህልና የቱሪዝም ተቋም እንደዚሁም በየሀገሩ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎችና አምባሳደሮች ስለ በዓሉ ታላቅነት፣ ተወዳጅነትና ዕሴት ያለማቋረጥ የማስተዋወቅ ሥራ በመስራታቸው ለመመዝገብ እንደበቃ ገልጸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በመኾኑም፣ የበዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ መመዝገብ ለዚህ ሃይማኖታዊ እና ሀገራዊ ተልእኮ ዕውቅና በመስጠት ረገድ የላቀ ሚና ስላለው ሃይማኖቱን፣ ባህሉንና ሥነ በዓሉን በማስተዋወቅ ሁሉም የበኵሉን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል። ሳምንቱ ለኢትዮጵያ ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩ ኢትዮጵያውያን ልሂቃን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝተው የተሸለሙበት መሆኑን ገልጸው፤ ''ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የዓለም የኖቤል ሽልማታቸውን ተቀዳጅተው ወደአገር በተመለሱበት ዕለት የበዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ መመዝገቡ ይፋ መኾኑ ልዩ ክሥተት ያደርገዋል'' ብለዋል። ''በከፍተኛው የዓለም ድርጅት ዕውቅና አግኝቶ የተመዘገበው የጥምቀተ ክርስቶስ በዓላችን፣ እናንተው የአባቶቻችኹን እምነት እና ባህል፣ ሥርዐት እና ታሪክ ጠብቃችኹ በየዓመቱ በምታከብሩት ውብና ሳቢ፣ ማራኪ እና ተወዳጅ የአከባበር ሥርዐት የተገኘ መኾኑን ተገንዝባችኹ በቀጣይነትም ከነበረው ምንም ሳይጓደል በየዓመቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ይጠበቅባችኋል'' ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ዩኔስኮ የቀረበለትን ሕጋዊ ጥያቄ በአዎንታ በመቀበል በዓለ ጥምቅተ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ስም በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ እንዲመዘገብ ውሳኔውን በማሳለፉ አባ ማትያስ አመስግነዋል። በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስ ከጥንት ጀምሮ ፍጹም የኾነ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመከባበር በዓል ኾኖ ሕዝቡን አንድ አድርጎና አስተሳስሮ የቆየ የአንድነት ማሕተም ስለኾነ፣ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ማኅበራዊ ዕሴቱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ አደራቸውን አስተላልፈዋል።