ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሽልማት እንደ አብነት በመውሰድ ሌሎች ድሎችንም ልንደግም ይገባል - ወጣቶች

ኢዜአ፤ታህሳስ 2/2012 የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሽልማት እንደ አብነት በመውሰድ ሌሎች ድሎችንም በተግባር ለመድገም መትጋት ይገባናል ሲሉ የመዲናዋ ወጣቶች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከትናንት በስቲያ በአገረ ኖርዌይ ኦስሎ ተገኝተው የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማታቸውን መቀበላቸው የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ማለዳ በድል ወደ አገር ቤት ሲመለሱም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ የጀግና አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ታዲያ የአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ ለመታደም ማልደው ወደ ስፍራው እያቀኑ ከነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች  መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች  ጠቅላይ ሚኒስትሩበአጭር ጊዜ ውስጥ በቁርጠኝነት በመስራታቸው ለድል መብቃታቸውን አውስተዋል።

ይህ ተግባራቸውም ከአገር አልፎ በዓለም አይን ውስጥ ያስገባቸውና ያሸለማቸው ተግባር መሆኑን ገልጸው፣ ወጣቶች ደግሞ አርአያቸውን በመከተል ''ድሉን በሌሎች አዳዲስ ድሎች ልንደግም ይገባል'' ብለዋል።

ወጣት ቤተልሄም እንዳለ በሰጠችው ሃሳብ ኢትዮጵያ አብዛኛው የህዝቧ ቁጥር በወጣቶች የተሸፈነ ቢሆንም አሁንም በድህነት የምትታወቅ ናት።

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተስፋና በትልቅ ተነሳሽነት በሰሩት ተግባር በድህነት የምትታወቀዋን አገር በሌላ መልካም ገጽታ አስጠርተዋታልና እኛም ይህን ፈለግ በመከተል ሌሎች ስኬቶች መስራት አለብን ብላለች።

ወጣት ደሳለኝ ወንዳለ በበኩሉ "ወጣቱ  አገርን በመስቀደምና ለጋራ ጥቅም በመተባበር ለሰላም ከሰሜን እስከ ምስራቅ፣ ከምዕራን እስከ ደቡብ ዘብ ልቆም ይገባል፤ በተነሳሽነትም መስራት አለበት" ባይ ነው።

ወጣት አብረሃም መንግስቴም በሰጠው ሃሳብ በተለይ ወጣቱ የእውነት ለውጥ ማምጣት ከፈለገ "በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በማይረቡ ሃሳቦች መጠመዱን ትቶ ለለውጥ በተግባር መሰለፍ" እንዳለበት ይናገራል።

ወይዘሮ ጥሩወርቅ አያለውም ለወጣቶች በስተላለፉት መልዕት " ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸው በወጣትነት እድሜ ደረጃ ያሉ መሪ ሆነው ሰርተው ያሳዩ በመሆናቸው ወጣቶች ተግባራቸውን መደገፍና መከተል ይገባቸዋል" ብለዋል።

በውጭ አገር ነዋሪ እንደሆኑ የገለጹት ወይዘሮዋ ወጣቱን በተግባር ለማገዝና አገርን በሚፈለገው ደረጃ በፍጥነት ለማሳደግ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በእውቀትና በገንዘብ በተቻላቸው አቅም ማገዝ እንደሚገባቸውም አክለዋል።

አገር ልታድግ የምትችለው በዜጎቿ በጋራ ቆሞ ማበርና መተባበር ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ። ነገ የምንፈልጋትን አገር ለመገንባት ዛሬን መስራት ይሻል ሲሉም ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

የዓለም የሰላም ሎሬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ በገቡት ቃል መሰረት በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ለ20 አመታት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ዳግም ለማስጀመር ባሳዩት ቁርጠኝነትና ባከናወኑት ተጨባጭ ተግባራት፣ እንዲሁም የፖለቲካ አስረኞችን በማስፈታት ባሳዩት ተግበር ሽልማቱን ሊያገኙ ችለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሸለሙት የሰላም የኖቤል ሽልማት  በዓይነቱ በዓለም 100ኛው ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም