ሽልማቱ ለዶክተር አብይ አህመድ መሰጠቱ ትክክለኛና የሚገባቸው ነው... አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ - ኢዜአ አማርኛ
ሽልማቱ ለዶክተር አብይ አህመድ መሰጠቱ ትክክለኛና የሚገባቸው ነው... አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ
ኢዜአ፤ታህሳስ 2/2012 የሰላም ኖቤል ሽልማቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሰጠቱ ትክክለኛና የሚገባቸው መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ አስታወቁ።
የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች የሰላም ኖቤል ሽልማት ላገኙት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ የደስታ መግለጫ ስነ ስርዓት አካሄደዋል።
በዚህ ስነስርዓት ወቅት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሸነፉበትን የሰላም ኖቤል ሽልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ክብር አብራርተዋል።
“ በሰላም እና መረጋጋት ያገኘውን አንፀባራቂ ድል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁላችንም በጋራ መስራት ይገባናል” በማለት፤ ሽልማቱም ለዶክተር አብይ መሰጠቱ ትክክለኛና ተገቢ እንደሆነ አስታውቀዋል።
"ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በሶማሌ ክልል ህዝብ ይደርስ የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የመልካም አስተዳደር ችግር በህግ አገባብ እንዲፈታ ለሰጡት አመራር እናመሰግናለን" ያሉት ደግሞ የፕሮግራሙ ተሳታፊ የሀገር ሽማግሌ አቶ መሀመድ አሊ መዶቤ ናቸው
ሼህ መሀመድ አብዲ የተባሉ ጂግጂጋ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው እንዳሉት በሶማሌና ኦሮሚያ ክልል ህዝቦች የነበረው የሰላም መደፍረስ እንዲወገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቁርጠኝነት ሰርተዋል።
“ሽልማቱ አንድነታቸውን አጠናክረን እንዲቀጥል አጋዥ ኃይል ይሆናል “ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያና በጎረቤት ሀገራት ሰላምና ብልፅግና እንዲረጋገጥ ላበረከቱት ስኬት ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘታቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል ።
በጅግጅጋ ከተማ በሚገኘው ቀልያን ዶዳን የህዝብ መሰብስቢያ አደራሽ በተካሄደው የደስታ መግለጫ ስነ ስርዓት አቶ ሙስተፌን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የኃይማኖት አባቶችና ሌሎችም ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።