ዛሬ የሚካሄደው የአልጀሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተቃውሞ ገጥሞታል

63

ኢዜአ፤ታህሳስ 2/2012 ለረጅም ዓመታት ሀገሪቱን የመሩት አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ  በተቃውሞ ከስልጣን ከወረዱ ከወራት በኋላ ዛሬ የሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ  ምርጫ ተቃውሞ እያስተናገደ ነው።

መራጮች ወደ ጣቢያዎች እየሄዱ ቢሆንም የድምፅ ሰጪዎች ቁጥር አነስተኛ እንደሚሆን ተንታኞች ገልፀዋል።

ለዚህም ምክንያቱ በሀገሪቱ ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ ተቃዋሚዎች በምርጫው እንደማይሳተፉ በመግለፅ በመቃወማቸው ነው ተብሏል።

ዛሬ በሚካሄደው ምርጫ የሚወዳደሩት አምስቱም እጩዎች ከስልጣን ከወረዱት ቡተፍሊካ ጋር ቅርበት ያላቸው የቀድሞ ባለስልጣናት መሆናቸውም ተሰምቷል።

ከዚህ ቀደም ቡተፍሊካ ለአምስተኛ ጊዜ በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶባቸው ከስምንት ወር በፊት ከስልጣን መውረዳቸው ይታወሳል።

በሀገሪቱ ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ካልተደረገ በስተቀር ምርጫ መካሄድ የለበትም በሚል ተቃዋሚዎች በየሳምንቱ አርብ በአደባባይ ድምፃቸውን ማሰማታቸውን አላቆሙም።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቡተፍሊካ የአገዛዝ ስርዓት እና ጊዜያዊ ፕሬዚዳንቱ አብደልቃድር ቤንሳላህ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ኑረዲን ቤዱዊን ጨምሮ የስርዓቱ አገልጋይ ባለስልጣናት ከመንበራቸው እንዲወገዱ የተቃዋሚዎች ፅኑ ፍላጎት ነው።

/ቢቢሲ እና ፍራንስ 24/

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም