የመሪ ከፍታ የአገርን ክብር ያንጸባርቃል...የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመሪ ከፍታ የአገርን ክብር ያንጸባርቃል...የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች
ኢዜአ ታህሳስ 2/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተሸለሙት የሠላም የኖቤል ሽልማት የደረሱበት የመሪነት ከፍታ የአገርን ክብር እንደሚያንጸባርቅ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ገለፁ። በተለያዩ መስኮች ፈር ቀዳጅ ተግባራትን ያከናወኑ ግለሰቦችና ተቋማት በየዓመቱ የሚሸለሙበት የኖቤል ሽልማት በዓለማችን ከሚሰጡ ዕውቅናዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በተለይም በዓለም ላይ ሰላም እንዲሰፍን ለጣሩና ውጤት ላስመዘገቡ የሚሰጠውን የሰላም የኖቤል ሽልማት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ማሸነፋቸው ይፋ ከተደረገ ሰንብቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የሠላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን ተከትሎ ከትናንት በስቲያ ሽልማታቸውን በኖርዌይ ርዕሰ መዲና ኦስሎ ተቀብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ለዚህ ሽልማት ያበቃቸው ወደ ስልጣን እንደመጡ በኢትዮጵያና ኤርትራ ለሁለት አስርተ ዓመታት "ሰላምም ጦርነትም የለም" በሚል መርህ የቆየውን የሁለቱን አገሮች የድንበር ግጭት በማስቆም ሠላም ለማውረድ ባደረጉት ጥረት እንደሆነም ተገልጿል። ይህን ተከትሎም በርካታ ኢትዮጵያውያን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የደስታ መግለጫ እና አስተያየት እየሰጡ ነው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በሰጡት አስተያየት፤ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡበት ወቅት አንስቶ እስከ አሁን በርካታ አስደናቂ ተግባራትን እያከናወኑ ናቸው" ብለዋል። ለአብነትም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ታጥሮ የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሰው ሰላምና ለውጥ እንዲመጣ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስታውሰው፤ ይህ ተግባር ደግሞ ለእርሳቸውም ሆነ ለአገር ኩራትና ክብር መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት። እርሳቸው ያመጡት ሽልማትም የበለጠ እንዲጠናከርና ኢትዮጵያ ወደ ተፈለገው ብልጽግና እንድትወጣ ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ ጥላቻን ማስወገድ እና ከልዩነት ይልቅ የጋራ የሚያደርጉ ነገሮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተናግረዋል። የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሸለሙት ሽልማት ለአገር ትልቅ ኩራት መሆኑን ገልፀው፤ ለመላ ኢትዮጵያውያንና አፍሪካዊያን የተሰጠ ክብር መሆኑንም ተናግረዋል። ሚኒስትሯ አክለውም ይህን የተሰጠንን ክብር ወስደን ወደ ተሻለ ከፍታ ለመጓዝም "እጅ ለእጅ በመያያዝ የዜጎችን ህይወት ለመቀየር መስራት አለብን" ብለዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ካሚል አህመድም የመሪዎች ከፍታ የአገርን ክብርና ገጽታ የሚያሳይ መሆኑን ገልፀው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ አንስቶ አለምን ያስደመመ ተግባራት እየከወኑ መሆኑን አንስተዋል። አሁን ላይ ያለውን ጥሩ ያልሆነ የማይመስል ድባብ ለማስተካከልም የአገር ገጽታ በማይበላሽ መልኩ "እርስ በእርስ ተደጋግፈን ልንሰራ ይገባልም" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተሸለሙት የሰላም የኖቤል ሽልማት በዓይነቱ በዓለም 100ኛው ነው ።