የብሄር ብሄረ ሰቦች እና ህዝቦች በዓል አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የብሄር ብሄረ ሰቦች እና ህዝቦች በዓል አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያስችላል
ኢዜአ ታህሳስ 2/2012 በየአመቱ ኅዳር 29 የሚከበረው የብሄር ብሄረ ሰቦች እና ህዝቦች ቀን አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። በዓሉ ኢትዮጵያውንያን አብሮነታቸውንና አንድነታቸው እንዲያጠናክሩ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳውም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አጽብሃ ተክለ እንዳሉትየበዓሉ መከበር ብሄሮችና ብሄረሰቦች ማንነታቸው፣ ባህል እና ቋንቋቸው ለማሳደግና አብሮነት ለማስቀጠል አግዟል።
ማንነትን በሚገልጽ ህብረ ብሄራዊ መንፈስ የሚከበረው በዓል የሀገር አንድነት እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው መምህር አጽብሃ ተናግረዋል።
''ዘንድሮ የተከበረው 14ኛው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ኢትዮጵያውን የፖለቲካ ልዩነት ሳይበግራቸው አንደነታቸው እና አብሮነታቸውን አንጸባርቀዋል'' ብለዋል።
''ይህም ላለፉት አመታት ያካበቱት ስነ ልቦናዊ አንድነታቸው መጠናከሩን እና እንደማይለያዩ ማሳያ ነው'' ብለዋል።
የዳበረ የፌዴራሊዝም ስርአት ለማስቀጠል በዓሉ ከፍተኛ ሚና አለው ያሉት መምህር አጽብሃ ባለፉት 27 አመታት የፌዴራል ስርአት ካመጣቸው ትሩፋቶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉ ኢትዮጵያውያን የበለጠ ተቀራርበው እንዲተዋወቁ እድል በመፍጠር የጠነከረች አገር ለመገባት ሚናው ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ በአክሱም ዩኒቨርስቲ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር መምህር ሓዱሽ ረዳኢ ናቸው።፡
''ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና የባህል ስብስቦች ለሚገኝባቸው አገሮች ሁነኛ የመንግስት መዋቅር ነው'' ብለዋል።
በዓሉ የፌዴራል ስርአት ትሩፋት መሆኑን ገልጸው የፌደራሊዝም ስርአት የራስ በራስ የማስተዳደር መብት በማክበር ሀገር በጋራ ለማልማት እና ለማስተዳደር ብሎም ህብረ ብሄራዊ እንድነት እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ተናግረዋል።
''ህገ መንግስታዊ እና ፌዴራላዊ ስርአት ኢትዮጵያን ከመበታተን የታደገ ስርአት ነው'' ብለዋል አቶ ሓዱሽ።
በዓሉ መከበሩም አንድነትን ከማጠናከር ባለፈ ህገ መንግስቱ የጸደቀበት ቀን በመሆኑ ለህገ መንግስቱ የላቀ ክብር የሚሰጥ መሆኑን መምህር ሓዱሽ ገልጸዋል።