የመብራት መጥፋትና መቆራረጥ ውጤታማ ሥራ ለመስራት እንቅፋት ሆኖብናል...በማህበር የተደራጁ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የመብራት መጥፋትና መቆራረጥ ውጤታማ ሥራ ለመስራት እንቅፋት ሆኖብናል...በማህበር የተደራጁ ወጣቶች
አምቦ ሰኔ 15/2010 የመብራት መጥፋትና መቆራረጥ ውጤታማ ሥራ ለመስራት እንቅፋት እንደሆናቸው በምዕራብ ሸዋ ዞን ሊበን ጃዊ እና ጨሊያ ወረዳዎች በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች ገለጹ፡፡ በሊበን ጃዊ ወረደ ባቢች ከተማ የወሊን የእንጨት እና ብረታ ብረት ኢንተርፕራይዝ ሊቀመንበር ወጣት አሰፋ ቦሩ በሰጠው አስተያየት በመብራት መቆራረጥ ምክንያት አብዛኛው ጊዜያቸውን ያለ ሥራ ያሳልፋሉ፡፡ የማህበሩ አባላት በ2008 ዓ.ም ወደ ሥራ ቢገቡም የመብራት መቆራረጥ ችግር ከዕለት ዕለት እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉና በዚህ ምክንያትም ሁለት ሠራተኞችን ከስራ ለማሰናበት መገደዳቸውን ገልጿል። የቶኩማ የእንጨት ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ ሊቀመንበር ወጣት ቶኩማ ጋዲሳ በበኩሉ ከተያዘው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ በከተማዋ በሚከሰት የመብራት መቆራረጥ ስራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንቅፋት እንደሆነባቸው ነው የተናገረው፡፡ ከደንበኛ የተቀበሉትን ሥራም በተስማሙበት ቀን ሰርተው ለማስረከብ ባለመቻላቸው በገቢያቸው ላይ ተጽዕኖ እያስከተለ መሆኑን አስረድተዋል። "ችግሩን ለመፍታት የሚመለከተው አካል በቅርበት ባለመኖሩና ዲስትሪክቱ በጌዶ ከተማ መገኘቱ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል" ብለዋል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል ችግራቸውን ተረድቶ ተገቢውን እልባት እንዲሰጣቸው ነው የጠየቁት፡፡ በተመሳሳይ በጨሊያ ወረዳ ጌዶ ከተማ በሴቶች የጸጉር ሙያ ሥራ ላይ የተሰማራችው ወይዘሪት ሌንሳ አባቡ "የመብራት መቆራረጥና መጥፋት በሥራዬ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል" ብላለች፡፡ በርካታ ደንበኞች እንዳሏት የገለጸችው ወጣቷ በአሁኑ ጊዜ የመብራት አገልግሎት አስተማማኝ ባለመሆኑ ደንበኞቿ እየራቋት በመሆኑ ገቢዋም እየቀነሰ መምጣቱን ገልጻለች፡፡ በከተማዋ በብረታ ብረት ሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት ሽመልስ ፈይሳ በበኩሉ "የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ በመጥፋቱ ምክንያት ሠርተን ገቢ ለማግኘትም ሆነ ከመንግስት የተበደርነውን ገንዘብ ለመክፈል አልቻልንም" ብሏል ። ለስምንት ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የገለጸው ወጣቱ ቀኑን ሙሉ መብራት በመጥፋቱ ምክንያት ለሠራተኞች የሚከፍለው ደመወዝ እያጠረው መምጣቱንም ተናግሯል። የሚመለከተው አካል አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ወጣቶቹ ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በምዕራብ አዲስ አበባ ሪጅን የጨልያ ዲስትሪክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሻምበል ከራ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የመብራት መቆራረጡ ችግር ምሰሶዎቹ አርጅተው በመውደቃቸው ምክንያት መከሰቱን አመልክተዋል። ችግሩን ለመፍታትም በአሁኑ ወቅት ያረጁ ምሶሶዎችን የመቀየር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።