ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ነገ ደማቅ አቀባበል ይደረግላቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ነገ ደማቅ አቀባበል ይደረግላቸዋል
ኢዜአ ታህሳስ 1/2012 የኖቤል የሠላም ሽልማታቸውን የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ነገ ጠዋት አዲስ አበባ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የተሸለሙት የኖቤል የሠላም ሽልማት የኢትዮጵያ ታሪክ በዓለም አደባባይ ጎልቶ እንዲነገር ማድረጉንም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ነገ ጠዋት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። አቶ ንጉሱ "ሁሉም ኢትዮጵያዊ በያለበት ለሠላም ዘብ በመቆም የሽልማቱን ዋጋ እንዲያጎላ" ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሽልማት የበቁት ከኤርትራ ጋር ለ20 ዓመት የዘለቀውን አለመግባባት በሠላም በመቋጨታቸው፣ በአፍሪካ ቀንድ ሠላም እንዲሰፍን ባበረከቱት አስተዋጽኦና ለሴቶች ተመጣጣኝ የፖለቲካ ስልጣን በማካፈላቸው እንደሆነ ሽልማቱ ሲበረከትላቸው ተገልጿል።