ጠቅላይ ሚኒስትሩ አለም አቀፍ እውቅና ማግኘታቸው ለኢትዮጰያውያን ትልቅ ኩራት ነው...ዶክተር አስራት አጸደወይን

ታህሳስ 1/2012 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ አለም አቀፍ እውቅና ማግኘታቸው ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ኩራት መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ገለጹ። የደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው የሰላም ኖቤል ሽልማቱ  ጠንክሮ ከተሰራ ለአለም የሚበቃ በጎ ተግባር ማበርከት እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል። ሽልማቱን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም በመሪነት ደረጃ ለሰላም ከፍተኛ ዋጋ ስጥተው ባደረጉት ጥረት በአለም አቀፍ መድረክ መሸለማቸው ልዩ ያደርጋቸዋል። ላለፉት 20 ዓመታት ሰላምም ሆነ ጦርነት የሌለበትን የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ፈር ቀዳጅ ወደ ሆነ የሰላም ስምምነት በማሸጋገር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማስጀመራቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ ኤርትራና ጅቡቲን በማስታረቅና በሌሎችም የቀጠናው ሀገራት ሰላም እንዲሰፍን ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ያደረጉት ጥረት ሌላው  ጥረት እንደሆነ ዶክተር አስራት ተናግረዋል፡፡ ሀገሪቱን ወደ አዲስ የፖለቲካ ለውጥ ምእራፍ በማሸጋገር የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዲቆም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና በውጪ የሚገኙ ተቃዋሚዎችም ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ጠቅሰዋል። እነዚህንና ሌሎችም ተዳምረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን በመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባስመዘገቡት ውጤት አለም አቀፍ እውቅና ማግኘታቸው ለኢትዮጰያውያን ትልቅ ኩራት መሆኑን ገልጸዋል። "ሽልማቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጭምር እውቅና የሰጠ በመሆኑ ለሰላም፣ ለልማት፣ ለሀገር ብልጽግናና እድገት ከመቼው ጊዜ በላይ አንድ ሆነን በጋራ ልንስራ ይገባል" ብለዋል። የኖቤል ሽልማቱ በማንኛውም ችግር ውስጥ ሆኖ ጠንክሮ ከተሰራ ለአለም የሚበቃ በጎ ተግባር ማበርከት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው ናቸው። "ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ ቆይታቸው ቀላል የመሰሉ ታላላቅ ስራዎችን ማከናወን ችለዋል" ብለዋል። የተበረከተላቸው ሽልማትም አለም ትኩረቱን ለኢትዮጰያ እንዲሰጥ ማስገደዱን አመልክተው  በቀጣይም የበለጠ ተበረታተው ታላላቅ ስራዎችን እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። ኢትዮጰያ ወደ ምትፈልገው አቅጣጫ እንድታመራ ቀን ከሌት እየታገሉ ያሉትን ዶክተር አብይ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ  ሁሉም ኢትዮጰያዊ ሊያግዛቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና የተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አስማረ መለሰ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆና የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆኑዋ ፈተናዎችን ማለፍ እንደሚቻል አመላካች ነው" ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ ሰላም እንዳይኖር የሚተጉ ኃይሎች የመኖራቸውን ያህል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላም ቁርጠኛ በመሆን ያስመዘገቡት አለም አቀፍ ክብርና እውቅና ለሰላም ፈላጊ ህዝቦች ኩራትና መመኪያ እንደሆኑ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ላበረከቱት በጎ አስተዋጽኦ ትናንት በኖርዌ ኦስሎ የሰላም ኖቤል ሽልማት እንደተበረከተላቸው ይታወቃል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም