የምግብ ዘይት በህገ ወጥ መንገድ አከማችቶ የተገኘ ግለሰብ ተያዘ

50
ኢዜአ ህዳር 30/2012 በቡኖ በደሌ ዞን ቦረቻ ወረዳ በህገወጥ መንገድ 2ሺ ሊትር የምግብ ዘይት በመኖሪያ ቤቱ አከማችቶ ተገኝቷል ያለውን ግለሰብ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ። ግለሰቡ የተያዘው በወረዳው ማዕከል በሆነው ያንፋ ከተማ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ነው። የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሳጅን ሰለሞን ዘውዴ እንደገለጹት ፖሊስ ጥቆማውን መሰረት በማድረግ ትናንት ማምሻውን ባደረገው ፍተሻ እያንዳንዳቸው 20 ሊትር የሚይዙ 100 ጀሪካን ዘይት በህገወጥ መንገድ በግለሰቡ መኖሪያ ቤት ተከማችቶ አግኝቷል:: ህጋዊ ፈቃድም ሆነ ሌላ ማስረጃ ሳይኖረው ዘይቱን አከማችቶ የተገኘው ግለሰቡ ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት ነው። ምርመራው እንደተጠናቀቀም ለፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ሳጅን ሰለሞን አስታውቀዋል። በአካባቢው በህገወጥ ንግድ የተነሳ ዘይትን ጨምሮ በአንዳንድ የሸቀጣ ሸቀጥ እና እህል ምርቶች እጥረት የዋጋ መናር እየተከሰተ መሆኑን ጠቁመዋል። ህብረተሰቡ ህገወጥ ንግድን ለመከላከል እያደረገ ያለውን ትብብር በቀጣይም አጠናክሮ እንዲቀጥል ሳጂኑ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም