በአማራ ክልል አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የተቀናጀ ስራ እየተካሔደ ነው - የክልሉ መንግስት - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የተቀናጀ ስራ እየተካሔደ ነው - የክልሉ መንግስት
ኢዜአ ህዳር 30 2012 .. በአማራ ክልል ዜጎች ያለስጋት የሚኖሩበትና ለልማት እንቅፋት የማይሆን የተረጋጋ ሰላም ለማስፈን ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለፀ። በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሳው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በክልሉ የተረጋጋ ሰላም ለማስፈን መንግስት አበክሮ እየሰራ ይገኛል። በተለይም ባለፉት ወራት በሁለተንተናዊ መንገድ ተሳስሮ ፣ ተዋልዶና ተዛምዶ የኖረውን የቅማንትና የአማራ ህዝብ ግጭት ውስጥ እንዲገባ ፍላጎት ያላቸው አካላት ሲራወጡ እንደነበር ተናግዋል። የተፈጠረውን ችግር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በመፍጠር የቀደመ ሰላሙን መመለስ እየተቻለ ነው ያሉት አቶ ጌትነት አሁንም እርቀ ሰላም የማስፈን ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በሌሎች አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን መጠነኛ ግጭትም በፀጥታ መዋቅሩ ጠንካራ እንቅስቃሴ መፍታት መቻሉን አስታውሰው ዘላቂነቱን ለማረጋገጥም አሁንም በትጋት እየተሰራ ነው ብለዋል ። የክልል መንግስት የፀጥታ መዋቅሩንና ህብረተሰቡን በማሳተፍ የዜጎችን ደህንነት በአስተማማኝ መልኩ ለመጠበቅና ለኢንቨስትመንት እንቅፋት የማይፈጥር ሰላም ለማስፈን በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል። ሰላምን የማስፈን ጉዳይ የመንግስት አጀንዳ ብቻ አለመሆኑን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ለሰላምና መረጋጋት የበኩሉን ሚና እንዲወጣም አሳስበዋል። በክልሉ በዘንድሮው የመኽር ወቅት አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን ጠቅሰው ህብረተሰቡን በማሳተፍም ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ የከፋ ጉዳት ሳይደርስበት መሰብሰብ መቻሉን አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅትም ተማሪዎችን፣ የፀጥታ መዋቅሩን፣ የመንግስት ሰራተኞችን፣ ወጣቶችንና ሌላውን ማህበረሰብ በማሳተፍ የደረሰውን ሰብል ከስር ከስር የመሰብሰብ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል ። በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረምም በሃይቁ ብዝሃ ህይወት ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ የ45 ቀናት የዘመቻ ስራ መጀመሩን ገልፀዋል። የጣና ሃይቅ ጉዳይ የክልሉ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጰያዊ ተስፋ የሆነው የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ጭምር በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል። በቀጣይ ወራትም የክልሉ መንግስት ሰላምና መረጋጋትን ከማስፈን ጎን ለጎን ሌሎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል። በተለይም የኢንቨስትመት እንቅስቃሴ፣ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ፣ የመስኖ ልማት ስራ ፣ የእንቦጭ አረም ማስወገድ ስራዎችና መሰል ተግብራት በተደራጀ አግበብ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቶ ጌትነት አስታውቀዋል።