በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ቢሻሻልም የመንጋ ፍትህ ሌላ ፈተና ሆኗል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ቢሻሻልም የመንጋ ፍትህ ሌላ ፈተና ሆኗል ተባለ
ኢዜአ ህዳር 30/2012 በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም መሻሻል እየታየበት መሆኑን የሰብዓዊ መብት ተቋማት ገለጹ።
ከለውጡ በኋላ የተለያዩ ህጎች እየተሻሻሉ መምጣታቸው እንደመልካም አጋጣሚ ቢቆጠርም የመንጋ ፍትህ አሁንም ስጋት ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ71ኛ ጊዜ የሚከበረው የሰብዓዊ መብቶች ቀን ዛሬ በአዲስ አበባ ከሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ የሲቪክ ማህበራት ጋር ተከብሯል።
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ መስዑድ ገበየሁ እንዳሉት፤ ከለውጡ በኋላ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ተስፋ ሰጭ ጉዳዮች ይታያሉ።
መንግስት ለሰብዓዊ መብት አያያዝ እንቅፋት የሆኑ የህግ ማዕቀፎችን በማሻሻልና ተቋማትን በማደራጀት ብዙ ርቀት ሂዷል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በሰብዓዊ መብት ጉዳይ የተሰማሩ የሲቪክ ማህበራት እንደጠላት ይቆጠሩ እንደነበር ገልጸው፤ አሁን መንግስት ለውይይት በሩን ክፍት ማድረጉን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ያለው አካሄድ በዜጎች ሰብዓዊ መብት ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊም አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
መንግስት ለሰብዓዊ መብት ትኩረት ሰጥቶ ተቋማትን ማደራጀቱና ህጎችን ማሻሻሉ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የውስጥ መፈናቀል፤ የመንጋ ፍርድ፣ መንግስት ህግ ለማስከበር የሚያሳየው ዳተኝነት ለዜጎች ስጋት መሆኑን አስረድተዋል።
"መንግስት ችግሮች ሲፈጠሩ በመዋቅራዊ ለውጥ ላይ ስለሆንኩ ነው በሚል የሚያቀርበው ሰበብ ጊዜ ሊቀመጥለት ይገባል፤ ሁልጊዜ ማሻሻያ በሚል ሰበብ ዜጎች መጎዳት የለባቸውም" ብለዋል።
በመሆኑም መንግስት የመንጋ ፍርድ እንዲቆምና ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ በነፃነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ እኛም የበኩላችንን ሚና እንወጣለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግሮች ቢኖሩም ለውጦች እንዳሉ ጠቁመዋል።
በማረሚያ ቤት የተጠርጣሪዎችና የታራሚዎች አያያዝ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅምና የዴሞክራሲ ዕድገት አንፃር ውስንነት ቢኖርበትም መልካም ጅምሮች እየታዩ ነው ብለዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በበኩላቸው መንግስት የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መዋቅራዊ ማሻሻያ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዜጎች በነጻነት የመደራጀት፣ የመሰብሰብና ሃሳባቸውን የመግለጽ መብታቸው እየተከበረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የታሰሩ ዜጎች መፈታታቸውንና ይሄን ተከትሎ ለእስር ይዳርጉ የነበሩ ህጎች በመሻሻል ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።