የአስጎብኚ ድርጅቶችን የደረጃ ምደባ ለማከናወን የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት መታቀዱ ተገለፀ

53
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 በቀጣዩ በጀት ዓመት የአስጎብኚ ድርጅቶችን የደረጃ ምደባ ለማከናወን የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት መታቀዱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ በስሩ የተመዘገቡ 580 አስጎብኚ ድርጅቶች መኖራቸውንም ነው ያስታወቀው። የሚኒስቴሩ የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ለኢዜአ እንደተናገሩት የደረጃ ምደባ በየትኛውም ዘርፍ መኖሩ ጥራትን ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው። በተለይም የአስጎብኚ ድርጅቶች የደረጃ ምደባ በመካከላቸው የጠነከረ የውድድር መንፈስ ከመፍጠር ባለፈ ያሉባቸውን ክፍተቶች ለመለየትም ይረዳቸዋል ብለዋል። ይህም በአገራችን ያለውን የቱሪዝም ዝቅተኛ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ይጠቅማልም ብለዋል። አስጎብኚ ድርጅቶችን በደረጃ ለመመደብ የሚያስችሉ አሰራሮች ለመዘርጋት በእንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህን ለመለየት የሚያስችል ረቂቅ መስፈርት መዘጋጀቱንም ተናግረዋል። በመስፈርቱ ላይ በአዲሱ በጀት ዓመት በዘርፉ ካሉ የንግድና የሙያ ማህበራት እንዲሁም አስጎብኚ ድርጅቶች ጋር ውይይት እንደሚደረግም ነው ያብራሩት። ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረገው ውይይት የጋራ ግንዛቤ ይዘን በሚቀጥለው ዓመት ስርዓቱን የመዘርጋት እቅድ እንደተያዘም ነው የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ። ስርዓቱ ከተዘረጋ በኋላ በተወሰኑ ድርጅቶች ላይ የሙከራ የደረጃ ምደባ ሊኖር እንደሚችልም ገልፀዋል፤ ከሙከራው ጠንካራና ደካማ ጎኑ ታይቶ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን በማውሳት። አስጎብኚ ድርጅቶች በበኩላቸው ደረጃ መኖሩ ዘርፉ በባለሙያ እንዲመራ በማድረግ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል። የፋም አቢሲኒያ የትራንስፖርትና ቱሪዝም ፐብሊኬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ማቲያስ ዲፒቶ እንዳሉት ደረጃዎችን መኖሩ ተወዳዳሪነትን እንደሚያጠናክርና  የሰለጠኑ ባለሙያዎችን እንዲመራ በማድረግ በተሻለ ጥራት የማስጎብኘት አገልግሎትን ማስኬድ ያስችላል ብለዋለ፡፡ የሳምንታ ቱር አስጎብኚ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሂሩት ገዛኸኝ እንደተናገሩት ሆቴሎችም የደረጃ ብቃት ቢሰጣቸው የተሻለ እንዲሰሩና የተሻለ የሰሩት ደግሞ እንዲበረታቱ ስለሚያደርግ ደረጃ መኖሩ ጥቅም አለው፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪስት ድርጅት ጋር በመሆን ከሚያዚያ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቱ የሚገኙ ሆቴሎችና ሪዞርቶችን በኮኮብ ደረጃ የመመደብ ስራ እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም