ሳዑዲ ዓረቢያ በኢትዮጵያ ቢዝነስ ዘርፍ ላይ ለሚሰማሩት ባለሀብቶች ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች - ኢዜአ አማርኛ
ሳዑዲ ዓረቢያ በኢትዮጵያ ቢዝነስ ዘርፍ ላይ ለሚሰማሩት ባለሀብቶች ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች
ኢዜአ ህዳር 30/2012 ሳዑዲ ዓረቢያ በኢትዮጵያ ቢዝነስ ዘርፍ ላይ ለሚሰማሩት ባለሀብቶች ድጋፍ እንደምታደርግ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አህመድ አብዱላዚዝ ገለጹ።
የኢትዮ-ሳዑዲ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በፎረሙ ላይ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የሳዑዲ ዓረቢያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ እና የሁለቱ አገራት የንግድ ልዑካን ቡድኖች ተገኝቷል።
የሳዑድ ዓረቢያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ አብዱላዚዝ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሁለቱ አገራት የቢዝነስ ግንኙነት ለማጠናከር አገራቸው ቁርጠኛ ናት።
የሳዑዲ ኢንቨስተሮችም በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በስፋት እንዲሰማሩ በቀጣይ የበለጠ ይሰራል ብለዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ወቅታዊ ሁኔታም ለአገራቱ ግንኙነት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በንግድና ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ለሚሰማሩት ባለሀብቶች የሳዑድ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብቷል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካሄል በበኩላቸው እየተሻሻለ በመጣው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ልክ ቢዝነሱን ለማጠናከር ብዙ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዝደንት ኢንጅነር መላኩ አዘዘው በሁለቱ አገራት መካከል የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የንግድ እና የቢዝነስ ስራዎች ላይ የበለጠ አብሮ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሚመክር ፎረም መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለቱንም አገራት ተጠቃሚ በሚያደርጉና ለአገሪቷ የገቢ ምንጭ ለማስገኘት የሚሰራ ስራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሁለቱ አገራት የረጅም ጊዜ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው አገራት ሲሆኑ 229 የሳዑዲ ዓረቢያ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የላከችሁ 40 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ከሳዑዲ ወደ አገር ያስገባችሁ ምርት ደግሞ የ187 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።