ቀጥታ፡

በትምባሆና በሺሻ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር በጸጥታ አካላት ትብብር ማነስ እየተስተጓጎለ ነው ተባለ

ኢዜአ ህዳር 30/2012''በትምባሆና በሺሻ ላይ የማደርገውን ቁጥጥር በአንዳንድ የጸጥታ አካላት ትብብር ማነስ ተስተጓጉሎብኛል'' ሲል የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒትና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ። ቁጥጥር ከተደረገባቸው 3 ሺህ 300 ካፌዎች፣ ባሮችና ሆቴሎች መካከል 600 የሚሆኑት የተከለከለ ተግባር ሲፈጽሙ ተገኝተዋል ባለስልጣኑ ከከተማው የምግብና መድሃኒት አስተዳደር ጋር በመተባበር በትንባሆና በሺሻ ላይ ድንገተኛ ቁጥጥር አድርጎ ውጤቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል። በኢትዮጵያ በ3 ሺህ 300 ካፌዎች፣ ባሮችና ሆቴሎች ላይ በተደረገ ቁጥጥር 600 የሚሆኑት የተከለከለ ተግባር ሲፈጽሙ መገኘታቸው ተገልጿል። በመግለጫው ወቅት የባለስልጣኑ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርቶች ደህንነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስናቀች አለሙ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ በተቋማት ላይ ድንገተኛ ቁጥጥር ለማድረግ በሚንቀሳቀስበት ወቅት የአንዳንድ ጸጥታ አካላት ትብብር ማነስ አጋጥሟል። ''ይህም ድንገተኛ ቁጥጥር በሚደረግባቸውና በህብረተሰቡ በሚደርስ ጥቆማ በህገወጦች ላይ የሚደረገውን ድንገተኛ ፍተሻ አስተጓጉሎብናል'' ብለዋል። ባለስልጣኑ በአዋጅ የተሰጠው ስልጣን እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን የጸጥታ አካላቱ ''የመበርበሪያ ማዘዣ ከፖሊስ ካላመጣችሁ'' በሚል ድንገተኛ ፍተሻው ሳይተገበር ቀርቷል። የቁጥጥር ስራው በልዩ ሁኔታና ድንገተኛ ጥቆማ ሲደርስ የሚተገበር በመሆኑ በቢሮክራሲ አሰራር ሳቢያ የተነሳ በአስፈላጊ ሰዓት ተገቢውን ተግባር ማከናወን እንዳልተቻለ ገልጸዋል። እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ በተለይ በቂርቆስና በልደታ ክፍለ ከተማ አንዳንድ ወረዳዎች ችግር በማጋጠሙ የሚፈለገው የቁጥጥር ስራ አልተከናወነም። ህግን የማስከበር ስራው እንዲሳለጠ የከተማው አስተዳደር ለሚመለከታቸው አካላት ትብብር እንዲያደርጉ መመሪያ እንዲሰጥ ባለስልጣኑ ጠይቋል። በቅርቡም በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ በአዲስ አበባ ብቻ  205 የሺሻ ዕቃ የተሰበሰበ ሲሆን 56  ተቋማት የጸሁፍና የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል። 10 ተቋማት ደግሞ ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት መላኩን ወይዘሮ አስናቀች ገልጸዋል። በአገሪቱ በ2008 ዓ.ም በተደረገ ጥናትም 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ በስራ ቦታና 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይና በቤት ውስጥ ለሁለተኛ አጫሽነት የተጋለጡ ዜጎች አሉ። በዓለም ላይ በየአምስት ደቂቃ ዘጠኝ የሚሆኑ ሰዎች ከትንባሆ ጋር በተያያዘ ይሞታሉ። በኢትዮጵያም በትንባሆና በሌሎች ሳቢያ የሚመጣውን ችግር ለመቀነስ የሁሉም ዜጋ ትብብርን ይጠይቃል። ባለስልጣኑም በቀጣይ በዩኒቨርሲቲዎችና በክልል ከተሞች የሚያደርገውን ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ወይዘሮ አስናቀች ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም