ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት መለኪያ ከ189 አገራት 173 ደረጃ ላይ ተቀምጣለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ልማት መለኪያ ከ189 አገራት 173 ደረጃ ላይ ተቀምጣለች
ህዳር 30/2012 የተባበሩት መንግስታት የልማት መርሃ ግብር ዛሬ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በፈረንጆቹ 2019 ዓ.ም ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሰብዓዊ ልማት በማስመዝገብ መጨረሻ ላይ ተቀምጣለች። የመንግስታቱ ድርጅት የልማት መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ዘመኑ የፈጠራቸውን ውስብስብ አካባቢያዊ ችግሮችን በአካባቢያዊ መፍትሄ መፍታት የሚያስችል አዲስ መርሃ ግብር ይፋ አድርጓል። የመንግስታቱ ድርጅት የልማት መርሃ ግብር ''ከገቢም፣ ከዓማካይ ስሌትም፣ ከዛሬም በላይ'' በሚል ርዕስ የሪፖርቱን ጥቅል ውጤት ይፋ አድርጓል። የሰብዓዊ ልማት መለኪያ ስሪት ጤናማና ረጅም እድሜ መኖር፣ እውቀትና የትምህርት ተደራሽነት እንዲሁም የነፍስ ወከፍ ገቢን መሰረት በማድረግ የሚሰላ ነው። በዚህ ስሌት መሰረት ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ከ2000 ዓ.ም ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል ብታሳይም አሁንም ብዙ ይቀራታል ተብሏል። የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቢሮ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ኃይሌ ክብረት እንዳሉት የአገሪቷ የሰብዓዊ ልማት ልኬቱ 0.470 በመቶ ላይ ይገኛል። ይህም ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን የሚናገሩት አማካሪው፤ ረጀም ዕድሜ በመኖር ረገድ ግን ከፍተኛ መሻሻል ታይቶ 66.2 ሆኗል ብለዋል። ከዚህ አንጻር ሴቶች 68.2 ዓመት በአማካይ ምድር ላይ መቆይት የቻሉ ሲሆን ወንዶች ደግሞ 64.4 ዓመት እየኖሩ መሆኑም በሪፖርቱ ተመልክቷል። በሌላ በኩል የአገሪቷ ዜጎች አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ 1ሺህ 782 የአሜሪካን ዶላር ሲሆን የትምህርት መጀመሪያ እድሜ ደግሞ 8.7 መሆኑን አብራርተዋል። ከዚህ ባለፈ ኢትዮጵያ በሁሉን አቀፍ የድህነት ልኬትም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን 83.5 በመቶ ዜጎቿ የሁሉን አቀፍ ድህነት ሰለባ ናቸው ብሏል ሪፖርቱ። 8.3 በመቶ ለተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች ያለት አገርና 27.3 በመቶ ዜጎቿ ደግሞ ከፍተኛ የገቢ ድህነት ውስጥ የሚገኙ መሆኑንም አቶ ኃይሌ ተናግረዋል። ከስርዓተ ጾታ እኩልነት አንጻርም ኢትዮጵያ ከ162 የዓለም አገራት ጋር ተነጻጽራ 123 ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በጥቅሉ ኢትዮጵያ ዓለም ከሚስማማባቸው የድህነትና የእኩልነት መለኪያ መስፈርቶች መሰረት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ነው አቶ ኃይሌ ያመለከቱት። ይህም ቢሆን ከ2000 ዓ.ም ወዲህ ኢትዮጵያ በብዙ ዘርፎች እምርታ ያሳየች ሲሆን በቀጣይም ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ትኩረት እድትሰጥ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል። የመንግስታቱ የልማት መርሃ ግበር የኢትዮጵያ ቢሮ ተወካይ ቱርሃን ሳሌህ በበኩላቸው ቀድሞ የሚታወቁ ችግሮች እንዳሉ ሆነው "ዓለም አዳዲስና ውስብስብ ችግሮች እየገጣማት ነው" ይላሉ። አዲሱ ትውልድ በብዙ መልኩ ኢፍትሃዊ ተጠቃሚ ስለመሆኑ ብዙ ምክንያቶች ቢጠቀሱም የአየር ንብረት ለውጥና ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ችግሮች ትልቅ ስፍራ አለቸው ብለዋል። የአሁኑ ድህነት ገቢ ከማግኘትም በላይ መሆኑን አበክረው የሚናሩት አቶ ቱርሃን፤ ከየትኛም ጊዜ በተሻለ ስለወደፊት ማሰብን ይጠይቃል ሲሉ ገልጸዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጊዜው እንዳልረፈደ በማወቅ ዘመኑን የዋጀ ፖሊሲዎችን አዘጋጅቶ ወደ ስራ ይገቡ ዘንድ ጠይቀዋል። በተመሳሳይም የልማት መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ ዘመኑ የፈጠራቸውን ውስብስብ አካባቢያዊ ችግሮችን በአካባቢያዊ መፍትሄ መፍታት የሚያስችል አዲስ መርሃ ግብር ይፋ አድርጓል። ''አክስለሬተር ላብ ኢትዮጵያ'' በተባለው ይህ መርሃ ግብር ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥያቄ ላለት ኢትዮጵያ ፍትሃዊ መፍትሄ መሆኑም ተመልክቷል። መርሃ ግብሩ ውስብስብ ችግሮችን በምን መልኩ መፍታት እንደሚቻል፣ አግባብነት ያለው መፍትሄ ማዘጋጀትና አካበቢያዊ መፍትሄን ከዘመናዊ አካሄድ ጋር አጣምሮ ይገዛል ነው የተባለው። ይህንኑ መርሃ ግብር የመንግስታቱ ድርጅት፣ የእስራኤል ተወካይ፣ የኮሪያ ዓለም ዓቀፍ የልማት ትብብር ተወካይና የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጋራ ለመስፈጸም ተግባበተዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚስትር ደኤታው አቶ ሲሳይ ቶላ መርሃ ግብሩ በተለይ ከፍተኛ ቁጥር ይዞ የሚገኘውን ወጣት ስራ ለማስያዝ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል። መርሃ ግብሩ አሁን ኢትዮጵያ የገጠማትን ውስብስብ የኢኮኖሚ ችግሮች መፍታት ይችል ዘንድም መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።