በአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ እየተዘረፉ መሆኑን አሽከርካሪዎች ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ እየተዘረፉ መሆኑን አሽከርካሪዎች ገለፁ
ኢዜአ፤ ህዳር30 / 2012 በአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ዝርፊያ እያጋጠማቸው መሆኑን አሽከርካሪዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በተደረገ የቅንጅት ስራ በአሁኑ ወቅት ድርጊቱ ቆሟል ብሏል።
ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የፍጥነት መንገዱ ተጠቃሚ አሽከርካሪዎች እንዳሉት አገልግሎቱን በሚሰጡበት ወቅት ዝርፊያ እየተፈፀመባቸው ነው።
አቶ ጥላሁን አድማሱ፣ አቶ ዱቤ ብርሃኑ እና አቶ ቸርነት እንድሪያስ የተባሉት አሽከርካሪዎቹ የፍጥነት መንገዱ መከፈቱ ጊዜያቸውን ከመቆጠብ፣ የመኪናውን ደህንነት ከመጠበቅና የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አኳያ ትልቅ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ መንገዱ እየሰጠው ካለው መልካም አገልግሎት በተጨማሪ አጥሩ በሚፈራርስባቸው አካባቢዎች ሰውና እንስሳት ወደ መንገዱ የመግባት ችግሮችም ስላሉ አጥሩን በማጠር በኩል ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ ከድር በበኩላቸው ችግሮቹ የታዩት በዋናነት በኦሮሚያ ክልል ግርግር ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ የአጥር መቁረጥና የብረት ስርቆት ሁኔታዎች በተደጋጋሚ እያጋጠሙ መሆናቸውን ገልጸው በነበረው ክትትል አጥር ሲቆርጡ እጅ ከፈንጅ ተይዘው እስከ ስድስት አመት የእስር ቅጣት የተፈረደባቸው አሉ ብለዋል።
ይሁን እንጂ የአጥር ብረቶችን እየቆረጡ የመውሰድ ወንጀሉ አሁንም መቀጠሉንና ከተማ ላይ ብረት የሚቀበሉ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ ከቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ጋር አብረን እየሰራን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በአሽከርካሪዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው ዝርፊያና የስርቆት ወንጀል ኦሮሚያ ክልል ተክስቶ ከነበረው ግርግር ጋር ተያይዞ የተከሰተ እንደነበረና ከሐምሌ እስከ ጥቅምት መጀመሪያ የታየ መሆኑን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ በቅርቡ በአሮጌው መንገድ ላይ በአንድ ከባድ መኪና ላይ ከተፈፀመው የዝርፊያ ወንጀል ውጭ በፍጥነት መንገድ ላይ ሲደረግ የነበረው ዝርፊያ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በተደረገው ቁጥጥር ሙሉ በሙሉ ቆሟል ብለዋል።