ቀጥታ፡

የኮምባይነር እጥረት ምርት አሰባሰቡን ፈታኝ አድርጎብናል - አርሶ አደሮች

ህዳር 30/2012 የኮምባይነር እጥረት ምርት አሰባሰቡን ፈታኝ እንዳደረገባቸው የሀድያ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ። ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በተለያዩ የግብርና ምርት አምራች አካባቢዎች መጠነኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። ምርትን ከዚህ ለማዳንም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ በደቡብ እና ሌሎች ክልሎችም የደረሱ ሰብሎችን የማሰባሰብ ተግባራት እየተከናወነ ነው። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ወደ ደቡብ የአገሪቷ ክፍል በመንቀሳቀስ የደረሱ ሰብሎችን አሰባሰብ ቅኝት አድርጓል። ምልከታው ከተደረገባቸው አካባቢዎች የሀድያ ዞን ሌሞ ወረዳ አንዱ ሲሆን፤ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ባቄላ አተርና ቦሌቄ በወረዳው ከሚመረቱ ምርቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። የወረዳው እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው ህዳር 10 እስከ 15  ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በተከታታይ ለአምስት ቀናት የጣለው ዝናብ መጠነኛ ጉዳት አድርሷል። በዚህም ስንዴ 17 ነጥብ 5 በመቶ፣ ጤፍ 25 በመቶ፣ ገብስ 12 ነጥብ 5 በመቶ፣ ባቄላ 20 በመቶ ፣ አተር 15 በመቶ፣ ቦሌቄ 15 በመቶ በአጠቃላይ 22 በመቶ ምርት ላይ ጉዳት እንደ ደረሰ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። አርሶ አደር ወርቅነህ ለንዴ በሌሞ ወረዳ ጀዌ ቀበሌ ስንዴን በኩታ ገጠም ከሚያመርቱት አንዱ ናቸው። ''ምርት ልንሰብስብ በተቃረብንበት ሰዓት ዝናብ ሳይጠበቅ መምጣቱ እጅግ አሳዝኖናል'' ያሉት አርሶ አደሩ ነገር ግን መንግሥት በባለሙያ እገዛ፣ በተማሪዎችና በሌሎች መንገዶች ያደረገውን ትብብር አመስግነዋል። የሀድያ ዞን የደረሰውን ሰብል ለማሰባሰብ የሰው ጉልበት ከመጠቀም በተጨማሪ 9 ኮምባይነሮችን ከባለሃብቶች ጋር በመደራደር እንዲገቡ አድርጓል። ይሁን እንጂ በርካታ ወረዳዎች ላሉት የሀድያ ዞን ዘጠኝ ኮምባይነር ማሰማራት በቂ እንዳልሆነ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ይናገራሉ። ለአብነትም ኢዜአ ተዘዋውሮ የጎበኘው 33 ቀበሌዎች ያሉት የሌሞ ወረዳ ላይ 2 ኮምባይነሮች ብቻ በኪራይ ምርት እንዲሰበስቡ ነው እያደረገ ያለው። አርሶ አደር ገዛኽኝ ከበደ በሰጡት አስተያየት በምርት አሰባሰብ ሂደቱ ኮምባይነር ግዜና ጉልበት ለመቆጠብ ቢያስችልም ከአርሶ አደሩ ብዛት ጋር ሲተያየይ የሚመጣጠን አይደለም ይላሉ። የሌሞ ወረዳ ሰቻ ሮማ ቀበሌ አርሶ አደር ደሳለኝ ደሎሬ በበኩቸው በቀበሌው ባለሙያዎች ቤት ለቤት እየሄዱ ድጋፍ እየሰጡን ነው ይላሉ። ከዚህ በፊትም ዋግ በሽታ በተከሰተ ወቅት መድሃኒት እንድንረጭ የባለሙያዎች ምክር ተከትለን ሰርተን ውጤታማ ሆነን ነበር፤ ነገር ግን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናቡ የተወሰነ ተጽእኖ አሳድሮብናል ሲሉ ተደምጠዋል። የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ጌታቸው ጋረደው በምርት አሰባሰቡ ሂደት በቀጣይም መንግሥት የሚሰጠውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። የሌሞ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ዳንኤል ላምብሮ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በ2011/2012 የምርት ዘመን በወረዳ ደረጃ 448 ሺህ 288 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር። ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የምርት ግኝቱ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ግምት እንዳለ የጠቆሙት ባለሙያው ዝናቡ ያስከተለውን ጉዳት ለማወቅ በተደረገ ግምገማ እስከ 86 ሺህ 454 ኩንታል ምርት ወደ ማጣት ደረጃ ተደርሷል ሲሉም ያብራራሉ። እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ ቀሪውን የደረሰውን ሰብል ለማሰባሰብ ባለሙያዎች በኩታ ገጠም የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ዘንድ በመሄድ ድጋፍ እያደረጉ ነው፤ ተማሪዎችም በምርት አሰባሰቡ ላይ እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው። አርሶ አደሩ የሚሰበስበውን ምርት በአግባቡ እንዲያስቀምጥም ምክረ ሀሳብ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። የሀድያ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን ኤርቆጮ እንደገለጹት በዞኑ በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው 127 ሺህ 900 ሄክታር መሬት ውስጥ 61 በመቶ ሰብል ተሰብስቧል። እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ የምርት አሰባሰቡ ሂደት ውጤታማ እንዲሆን ባለሙያዎች በተለያዩ ወረዳዎች እየተዘዋወሩ የትኛው አካባቢ ምርት ደርሷል? ምን አይነት ሰብል ነው? እንዴት ሊሰበሰብ ይገባል? የሚለውን ሙያዊ እገዛ እያደረጉ ነው። የሰብል አሰባሰብ ዘመቻውን የሚመራና በዞን አስተዳዳሪ የሚመራ ግብረ ኃይል መቋቋሙን የገለጹት ኃላፊው ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ዞን ድረስ በየቀኑ የአሰባሰቡን መረጃ እንደሚለዋወጡም ጠቁመዋል። በተለይም የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶችና የኃይማኖት ተቋማት በበኩላቸው ድጋፍ እየሰጡ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነም ነው የጠቆሙት። ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ማሽንን ከመጠቀም አንጻርም በአምስት ወረዳዎች ላይ በኮምባይነር በመጠቀም ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል። አርሶ አደሮች ያነሱት ምርት መሰብሰቢያ ማሽን ኮምባይነር እጥረት ትክክል መሆኑን የገለጹት አቶ ካሳሁን እጥረቱ ግን በአገር አቀፍ ደረጃ ያለ መሆኑንና አሁን እየቀረበ ያለውም ከባለሃብቶች ጋር በመደራደር እንደሆነ ምላሽ ሰጥተዋል። የኮምባይነር እጥረቱን በዘላቂነት ለመፍታት ግን መንግሥት የግብርና ግብዓቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ በተዘረጋው አሰራር መሰረት ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶችና የገበሬዎች ኀብረት ስራ ማህበራት ማሽኖችን እንዲያስገቡ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም አመልክተዋል። በሀድያ ዞን በ2011/2012 የምርት ዘመን ዋና ዋና ሰበሎችና የፍራፍሬ ምርቶችን ጨምሮ 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም