ቀጥታ፡

ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ ሁለት ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀረቡ

ኢዜአ፤ ህዳር 29 / 2012 የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ ሁለት ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀረቡ። በእስር ላይ የሚገኙት ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ አራት ግለሰቦች ከራዳር ግዥ ጋር በተያያዘ ያለአግባብ በባከነ የ214 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ሕዳር 17 ቀን 2012 ዓም ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወቃል። ግዥው የተካሔደው የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሳይፈልግና ሳይጠይቅ እንዲሁም መመሪያን በመጣስ የጦር መሣሪያ ራዳር ግዥ በመፈጸም በመንግሥት ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስ በሚል ነው ክሱ የተመሰረተው። በክስ መዝገቡ የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ የሃይቴክ ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ ሌተና ኮሎኔል ፀጋዬ አንሙት፣ የቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታና የሥነ ምግባርና የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል መሐመድ ብርሃን ኢብራሒም/ያልተያዙ/ ይገኙበታል፡፡ ተከሳሾቹ ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው ግዥው እንዲፈጸም ያደረጉት ራዳር ከመከላከያ ሠራዊት የትጥቅ ደረጃ አንፃር ዘመናዊ ያልሆነ፣ ለኢትዮጵያ መልክዓ ምድር የማያገለግል መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም ሰውን፣ እንስሳትንና ሌሎች ግዑዝ ነገሮችን የማይለይ፣ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የሚያስቸግርና ሠራዊቱ ያለበት ሥፍራ የኤሌክትሪክ ኃይል የሌለበት በመሆኑ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ መሆን ሲገባው በኤሌክትሪክ ቻርጅ የሚሠራ መሆኑንም አክሏል፡፡ በመሆኑም ለሙከራ ቀርበው የነበሩ ራዳሮች እንደማይሆኑ ከሠራዊቱ አስተያየት ተሰጥቶባቸው እያለ፣ 111 ራዳሮች ያለአግባብ ተገዝተው ያለ አገልግሎት በሃይቴክ ኢንዱስትሪ መጋዘን ውስጥ እንዲቀመጡ  መደረጋቸውን አስረድቷል፡፡ ተከሳሾቹ በፈጸሙት የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ተከሳሾቹ የክስ መቃወሚያ ካላቸውም ለመጠባበቅ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት ለዛሬ ሕዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዞ ነበር። በዚህ መሰረትም የአንደኛ ተከሳሽ ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ጠበቃ ጉዳዩን በዝርዝር ለማየትና መቃወሚያ ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ ጠይቀዋል። ሁለተኛ ተከሳሽ ሌተና ኮሎኔል ፀጋዬ አንሙት ደግሞ የክስ መቃወሚያ እንደሌላቸው ገልፀው ድርጊቱ ተፈጽሟል ወንጀለኛ ግን አይደለሁም ሲሉ የእምነት ክሕደት ቃላቸውን ሰጥተዋል። "በተመደብኩበት የስራ መስክ ኃላፊነቴን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተወጥቼያለሁ ወንጀለኛ ሊያስብለኝ የሚያስችል ተግባር አላከናወንኩም" በማለት ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል። ሶስተኛ ተከሳሽ ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታ ደግሞ በመታመማቸው ምክንያት ያልቀረቡ ሲሆን ፖሊስ አራተኛ ተከሳሽን ይዞ ለማቅረብ ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ነው የጠየቀው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም