ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት እንዳልቀነሰ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት እንዳልቀነሰ ተገለጸ
ኢዜአ 30/2012 ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መልካቸውን በመቀየር እየተባባሱ መምጣታቸውን የሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴር ገለጸ። ''ሴቶችንና ህጻናትን ከጥቃት በመጠበቅ ሃላፊነታችንን እንወጣ'' በሚል መሪ ሃሳብ ከህዳር 15 ቀነ 2012ዓም አንስቶ ሲከበር የቆየው የነጭ ሪቫን ቀን ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ28ኛ ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ ተከብሮ በቆየው ማጠቃለያ ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የሴቶችና ህጻናት ሚኒስትሯ ወይዘሮ አለም ጸጋይ ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መልካቸውን በመቀየር እየተባባሱ መምጣታቸውን ተናግረዋል። በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ታዲያ ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዞውን ወደ ኋላ እንደሚጎትቱ እሙን ነው ብለዋል። በመሆኑም ይህን ጥቃት ለመከላከል ጠንካራ ህግ ማውጣትና አፈጻጸማቸውን መከታተል የሁሉም ሃላፊነት መሆን እንዳለበትና የወንዶች አጋርነትም መጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል። አያይዘውም የኃይማኖት አባቶች ጾታዊ ጥቃትን ለማስቆም እና እሴቶቻችንን በመገንባት ረገድ ትልቅ ድርሻ ስላላቸው ይህንን ማህበራዊ ሚና እንዲወጡ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል። በመዲናዋ ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ተጠቂዎች ጋንዲ፣ ሚኒልክ እና ጥሩነሽ ቤጅንግ ሆስፒታሎች ተገቢውን ድጋፍ እየሰጡ ነውም ብለዋል። በ2011 ዓ.ም ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ህክምና ማእከሉ የመጡት 3 ሺህ ሴቶች ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ 150ዎቹ ከአራት አመት በታች ያሉ ህጻናት መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ኃላፊ ውይዘሮ አልማዝ አብርሃ ናቸው። በመሆኑም "ጾታዊ ጥቃቱ መልኩን እየቀየረ መጥቷል እንጂ ጥቃቱ ምንም አይነት መቀነስ አላሳየም" ብለዋል። ጥቃት ሲፈጸም የአንድ ሳምንት የተቃውሞ ዘመቻ ብቻ ይደረግና መልሶ መቀዛቀዝ ስለሚያሳይ ጥቃቱን ማስቆም አልተቻለም ሲሉ ወይዘሮ አልማዝ ተናግረዋል። ይኸን ጥቃት ለመከላከልና ለማስቆም ታዲያ የሁሉም ዜጋ አስተሳሰብ መዳበር አለበት ተብሏል። በተለይም በአካል ጉዳተኛ ሴቶችና ህጻናት ላይ በርካታ ጥቃት እየተፈጸመ እንደሆነና፤ ጥቃቱም የሚፈጸመው በቅርብ የቤተሰብ አባል መሆኑን ተከትሎ ህብረተሰቡ እንዳይማርበትና ጥንቃቄ እንዳይደረግ አድርጎታልም ተብሏል። በዓለማችን 35 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ጻታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው የአለም የጤና ድርጅት ያደረገው ጥናት ያሳያል።