የሐይማኖት አባቶች በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
የሐይማኖት አባቶች በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ገለፁ
ህዳር 30/2012 በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ የምዕራብ አርሲ ዞን የሐይማኖት አባቶች ገለፁ ፡፡ የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በምዕራብ አርሲ ዞን ከሚገኙ የሐይማኖት አባቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር የሠላምና አብሮነት አስተማህሮቶችን የተመለከተ ጉባኤ በሻሸመኔ ከተማ አካሂዷል፡፡ የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ የህዝብ ግንኙነትና ዶክመንቴሽን መምሪያ ኃላፊ ሀጂ መንስኡድ አደም የሠላም ጉባኤው በዋናነት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሐይማኖትና የብሔር ብዝሀነትን ለማስተዳደር የሐይማኖት መሪዎችና ሌሎች የማህበረሰቡ ክፍሎች ያላቸውን ሚና የተመለከተ እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡ ''ብዝሀነት ተፈጥሯዊ በመሆኑ በፀጋ ልንቀበለው ይገባል'' ያሉት ሀጂ መንስኡድ አሁን ላይ በሀገሪቱ ውስጥ እየታዩ ያሉ ከዚህ እሳቤ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች በሐይማኖቶች አስተምህሮትም ሆነ በባህል ፍፁም ተቀባይነት የሌላቸው እንደሆኑ ነው የገለፁት ፡፡ ከዚህ ችግር ለመውጣት እርስ በእርስ መከባበርና መደማመጥ እንደሚያስፈልግ ገልፀው የሐይማኖት መሪዎች ሠላምና አብሮነትን ለማስፈን መጫወት ስለሚገባቸው ሚና የጋራ መግባባት ለመፍጠር ታልሞ ጉባኤው መዘጋጀ አስረድተዋል ፡፡ ይህ የሠላም ጉባኤ በምዕራብ አርሲ ዞን ተፈጥሮ የነበረውን ሐይማኖት መልክ ያለው ግጭት በዘላቂነት ለመፍታትና የህዝቡን አብሮነት ለማስቀጠል ታስቦ መዘጋጀቱን ገልፀው የኢትዮጵያ ሐይማኖት ጉባኤ መሰል መድረኮችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እያካሄደ መቆየቱን ሀጂ መንስኡድ ተናግረዋል ፡፡ የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በየደረጃው ካሉ የአስተዳደር አካላት ፣ የጉባኤው መዋቅሮች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አካላት ጋር የሠላምና አብሮነት እሴቶችን የሚያጠናክሩ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም አክለው ገልፀዋል ፡፡ ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል የምዕራብ አርሲ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፀሐፊ እንዲሁም በዶዶላ ከተማና አካባቢው የዕምነቱ መሪ የሆኑት ሼህ ሀቢብ ሁሴን እስልምና የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳሆኑ ሌሎችም ሠላም እንዲሆኑ የሚያስፈልገውን ሁሉ በማድረግ የሚሰብክ አስተምህሮት እንዳለው ተናግረዋል ፡፡ የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሠላምና አብሮነት አስተምህሮቶች በተመለከተ የተለያዩ ቤተ እምነቶችን በማሰባሰብ ያዘጋጀው መድረክ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው እንደሆነም ገልፀዋል ፡፡ በምዕራብ አርሲ ዞን በተለይ ዶዶላ ከተማ ሁከት በተፈጠረበት ወቅት በቦታው እንደነበሩ የሚናገሩት ሼህ ሀቢብ ችግሩ የሐይማኖትና የብሔር ሽፋን ይሰጠው እንጂ በሐይማኖቶችና በብሔሮች መካከል የተፈጠረ ፀብ እንዳልነበረ ገልፀዋል ፡፡ ነገር ግን የራሳቸውን አጀንዳ በህዝቡ መካከል ለማስረጽ የሚፈልጉ ኃይሎች ክስተቱን እንደመልካም አጋጣሚ እንደተጠቀሙበት ነው ያስረዱት ፡፡ በወቅቱ ሁከቱን ለማብረድ ከፀጥታ ኃይሎችና ከሌሎች የሐይማኖት አባቶች ጋር በመሆን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸውንም ተናግረዋል ፡፡ ከሁከቱ በኋላም እንደዚሁ ህዝቡን ለማቀራረብና እርቀ ሰላም እንዲወርድ ለማድረግ በርካታ ተግባራትን በጋራ ማከናወናቸውንና ይህም ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል ፡፡ ዘለቄታ ያለው ሠላም ማስፈን የሚቻለው በእምነቱ የታነፀ ማህበረሰብ መፍጠር ሲቻል ነው ያሉት ሼህ ሀቢብ በዚህ ላይ የሐይማኖት አባቶች ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል ፡፡ በአካባቢው ተከስቶ የነበረው ችግር ሙሉ በሙሉ ተወግዶ ዘላቂ ሠላምና አንድነት እንዲሰፍንም የሚጠበቅባቸውን ውሉ እንደሚያደርጉ ነው ያስረዱት ፡፡ በምዕራብ አርሲ ዞን የዶዶላ ወረዳ የደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ምህረት ቀሲስ ደምሰው በየነ በበኩላቸው አባቶች ለምዕመናኑ ስለ ሠላምና አንድነት ማስተማር ሐይማኖታዊ ግዴታችንም ጭምር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የሐይማኖት አባቶች ስለእምነታቸው ብቻም ሳይሆን ስለ ሀገርም መቆርቆር እንደሚገባቸውም ገልፀዋል ፡፡ ''አብዛኛው የዶዶላ አካባቢ ነዋሪዎች በሐይማኖትም ሆነ በብሔር ተቀይጠው አብረው የሚኖሩ ናቸው'' ያሉት መልዐከ ምህረት ቀሲስ ደምሰው የተከሰተው ችግርም እንደዚሁ ለይቶ ለመፈረጅ የሚያስቸግር እንደሆነ ነው የገለፁት ፡፡ ካለፈው ክስተት በመማር ለወደፊቱ ትውልዱን በተስተካከለ መንገድ ለመቅረፅ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡም አስረድተዋል ፡፡ በሠላም ጉባኤው በምዕራብ አርሲ ዞን የሚገኙ የሐይማኖት መሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል ፡፡