ወጣቶች የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዲጠበቁና እንዳይጣሱ ገንቢ ሚና መጫወት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዲጠበቁና እንዳይጣሱ ገንቢ ሚና መጫወት አለባቸው
ኢዜአ ህዳር 29 / 2012 ዓ.ም ወጣቶች የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዲጠበቁና እንዳይጣሱ ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰብአዊ መብቶች ማዕከል ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን በፓናል ውይይት አከበረ። በፓናል ውይይቱ እንደተነሳውም ወጣቶች በሚፈጠሩ ግጭቶች ውስጥ ተሳትፈው መጠቀሚያ እንዳይሆኑና ወደ መጥፎ ተግባራት እንዳይገቡ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ማግኘት አለበት ተብሏል።
እ.አ.አ በ1948 የጸደቀውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ለማስታወስ በየዓመቱ ታህሳስ 1 የዓለም የሰብአዊ መብቶች ቀን ይከበራል።
"ወጣቶች ለሰብዓዊ መብቶች ዘብ መቆም አለባቸው" የሚለው ደግሞ ነገ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን መሪ ሐሳብ ነው።
ቀኑን አስመልክቶ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው የፓናል ውይይት ሁለት የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ሰፋ ያለ ወይይት ተደርጎባቸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የሶስተኛ ዲግሪ የህግ ተማሪ ደጀን የማነህ ወጣቶች የሰብአዊ መብቶችን ብቻ ማክበር ብቻ ሳይሆን ለአገር ሰላምና ልማት ያላቸው ሚና ወሳኝ እንደሆነ ይገልጻል።
አሁን ለመጣው ለውጥም ወጣቶች ለሰብአዊ መብት መከበርና ሌሎች ጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲያገኙ ያደረጉት ትግል ውጤት እንደሆነ ተናግሯል።
"አሁንም ወጣቶቹ በመጀመሪያ ደረጃ ወደ ጎዳና ለተቃውሞ የወጡባቸው ምክንያቶች በመንግስት በበቂ ሁኔታ ምላሽ እያገኙ አይደለም" ብሏል።
የህግ ተማሪው አክለውም አሁን ባለው የለውጥ አመራር ውስጥም ወጣቶች ያላቸው ተሳትፎ አመርቂ እንዳልሆነና የወጣቱ ትግል ወደ ባለቤትነት እንዳልተሸጋገረ አንስተዋል።
ሁልጊዜ ወጣቱ ለኢትዮጵያ እድገትና ልማት ወሳኝ ነው ይባል እንጂ በተጨባጭ ግን በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና ማህበራዊ መስኮቹ የወጣቱ ተሳትፎ እምብዛም እንደሆነ ነው ተማሪ ደጀን የሚገልጸው።
አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸሙ ላሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ወጣቱን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አግባብ እንዳልሆነና ከጀርባ ሆነው ወጣቱን መጠቀሚያ እያደረጉ ያሉ አካላት ለህግ መቅረብ እንዳለባቸውም አክለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግና የአስተዳደር ጥናቶች ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ደመላሽ ሽፈራው በበኩላቸው "ወቅታዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ወጣቱን የግጭቶች መጠቀሚያ እያደረገው ነው" ብለዋል።
ወጣቶች ወደ ግጭት በመግባት የሚፈጽሙት ተግባር የሰብአዊ መብቶች እንዲጣሱ እያደረገ እንደሆነና ይሄም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
አሁን ያለውን ፖለቲካዊ ከባቢ ሁኔታን ማስተካከል ወጣቶች ወደ ግጭቶች እንዳይገቡ ከማድረግ አኳያ ወሳኝ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የህግና የአስተዳደር ጥናቶች ትምህረት ክፍል ዲን ዶክተር ሰለሞን ንጉሴም መንግስት ለወጣቶች ጥያቄ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት አለበት ይላሉ።
የስራ አጥነት ችግርን መፍታት ወጣቱ ጥራት ላለው ትምህርት ያለውን ተደራሽነት ማስፋት እና የወጣቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ወጣቶች መብት እንዳላቸው ሁሉ ግዴታንም መወጣት እንደሚገባቸውና ጥያቄያቸውን በሰከነና በተደራጀ መልኩ ማቅረብ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰአት በወጣቶች ውስጥ ያሉትን ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ወደ መደበኛ አደረጃጀት ማምጣትና ለሰብአዊ መብቶች መከበር ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ለሰብአዊ መብቶች መከበር እሳት የማጥፋት ስራ ሳይሆን ዘላቂና መግባባትን ያዘለ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ይሄም በአንድ ጀምበር የሚመጣ ሳይሆን ጊዜ የሚወስድ ጉዳይ እንደሆነ አንስተዋል።
የፖለቲካው ባህል ከጽንፈኝነትና የእኔ ብቻ ሀሳብ ይደመጥ ከሚለው አስተሳሰብ ወጥቶ ወደ መደማመጥና የጋራ መግባባት ባህል መምጣት እንዳለበትም ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝም ተቋም ሃላፊ ዶክተር ዘመልዓክ አየለ በበኩላቸው ለሰብአዊ መብቶች መከበርና መጠበቅ ታች ያሉ የመንግሰት አስተዳደር መዋቅሮችን አቅም ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በየዞኑ በየወረዳውና በየቀበሌው የሚገኙ አመራሮች ወጣቱን የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ በማድረግ ወጣቱ ወዳልተፈለገ ተግባር እንዲገባና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን እንዲፈጽም እያደረጉ ነው ብለዋል።
የፌደራል መንግስቱ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የታችኛው የመንግስት አስተዳደር ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንዲሁም አመራሮችም በሰብአዊ መብት ጥበቃና መከበር ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ አንዳለባቸው ገልጸዋል።
ነገ ለ71ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን በኢትዮጵያ ለ13ኛ ጊዜ "ወጣትነት ለሰላምና ለሰብአዊ መብቶች" በሚል መሪ ሐሳብ ይከበራል።
እ.አ.አ በ1948 በፓሪስ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ሲጸድቅ ከአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ ላይቤሪያና ግብጽ በወቅቱ መፈረማቸው ይታወሳል።
ኢተዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌን በማጽደቅ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ ያካተተች ሲሆን በህገ መንግስቱ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት አንቀጾች የሰብአዊ መብቶችን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ያካተተ ነው።