ቀጥታ፡

የመደመር እሳቤ ብሄር ብሄረሰቦች ጠንካራ የጋራ ማነነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው ተባለ

ኢዜአ ህዳር 29 / 2012 ዓ.ም የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጠንካራ የጋራ ማንነት እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ። 14ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዛሬ በአዲስ አበባ ተከብሯል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች የመደመር እሳቤ ብሄር ብሄረሰቦች ጠንካራ የጋራ ማንነት እንዲገነቡ የሚያደርግ መሆኑን ነው የገለጹት። ከስልጤ ዞን የመጡት ወይዘሮ አሚና ሽኩራ ልዩነት ውበት ቢሆንም ከልዩነት ይልቅ አገራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል። መደመር ልዩነትን አቻችሎ በጋራ ጉዳይ ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ለአገሪቷ ሰላምና ልማት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ወይዘሮ አሚና ገልጸዋል። ከጋሞ የመጡት አቶ መላኩ ጦቾ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ያለመግባባት ችግሮች አገራዊ አንድነቱን የሚሸረሽሩ ናቸው ብለዋል። የመደመር እሳቤ ቂምና ጥላቻን ትተን ለይቅርታ ልባችንን መክፈት የሚያስችል ነው ሲሉም ተናግረዋል። የመደመር እሳቤ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ማረጋገጥ እንዳለበት የምትገልጸው ደግሞ ከትግራይ ክልል የመጣችው ወጣት እርጋታ አባዲ ናት። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ብሄር ተኮር ግጭቶችና አለመግባባቶች አገራዊ አንድነትን የሚያዳክሙ መሆናቸውንም አንስታለች። ህገ መንግስቱ ከጸደቀ 25ኛ ዓመቱ ላይ የተከበረው የዛሬው በዓል ''ህገ-መንግስታዊ ቃልኪዳናችን ለዘላቂ ሰላማችን'' በሚል መሪ ቃል ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም