ዜጎች ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና እምነት ሲጎለብት የአገራቸው ሰላም ያብባል---ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
ዜጎች ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና እምነት ሲጎለብት የአገራቸው ሰላም ያብባል---ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ
ኢዜአ ህዳር 29 / 2012 ዓ.ም ዜጎች ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና እምነት ሲጎለብት የአገር ሰላምና ምጣኔ ሀብት አቅም እንደሚጎለብት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
በ14ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ዛሬ በአዲስ አበባ ተከበሯል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተከበረው በዓል ላይ ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ እንደተናገሩት የዜጎች የአገር ፍቅርና እምነት መጎልበት የአገር ሰላም እንዲያብብና የኢኮኖሚ አቅም እንዲያድግ ያደርጋል።
ህዝቦች ከግጭት ርቀው ማህበራዊ መስተጋብራቸው እንዲጠናከርም እገዛ እንዳለው ተናግረዋል።
ይህም የኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞ ያለ እንቅፋት እንዲቀጥል እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።
“አንድነታችንን ጠብቀን በኢትዮጵያችን ህልውና ሳንደራደር እስከተነሳን ድረስ ምንም ኃይል ሊያቆመን እንደማይችል እርግጠኞች እንሁን" ሲሉም ፕሬዝደንቷ ተናግረዋል።
የዘንድሮው የበዓሉ አዘጋጅ የሆነው ክልል የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዝደንት ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ” ባለፈው ዘመን ካለፍንበት ውጣ ውረድ ይልቅ ከፊታችን ያለው ዘመን ይበልጣል“ ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም ያለፍንባቸው መንገዶች ላይ ትኩረት ከመስጠትና ከ’ ቆሞ ቀርነት’ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ ፌዴራላዊ ስርዓቱ በወንድማማችነት ጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆምና ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ እንዲያደርግ መትጋት ያስፈልጋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም እንደገለጹት "የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ብዝሃነታችንን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከያዝነውና ካስተናገድነው የውበትና የጥንካሬ መሰረት መሆኑን ማሳያ ነው" ብለዋል።
የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል የብሄር ብሄረሰቦችን አንድነት፣ እኩልነትና ኩራት ማሳያ በመሆኑም ማስቀጠል እንደሚገባ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መረጋገጡንም አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል።
የ14ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን "ሕገ-መንግስታዊ ቃልኪዳናችን ለዘላቂ ሠላማችን" በሚል መሪ ሐሳብ በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በአዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ ተከብረዋል።