ህብረተሰቡ ጽንፈኞችን በመታገል የድህነት ትግሉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ ጽንፈኞችን በመታገል የድህነት ትግሉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ
ኢዜአ ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም ሕብረሰተቡ ለውጡን የማይፈልጉ ጽንፈኞችን በመታገል ሃብት እና ጊዜውን ለጸረ ድህነት ትግሉ እንዲያውል ጥሪ ቀርበ፡፡ 14ኛው የብሔር ብረሰቦች ቀን በአሶሳ ከተማ ዛሬ በደማቅ ስነ-ስርዓት ተከብሯል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ በዚህ ወቅት እንዳሉት አገራዊ ለውጡን የማይፈልጉ ጥቅማቸው የተነካባቸው ጽንፈኛ ኃይሎች የሚያሰራጯቸውን መረጃዎች ህብረተሰቡ በጥንቃቄ ማየት አለበት፡፡
“ለውጡን ተከትሎ ያጋጣሙ ፈተናዎችን ማለፍ ጀምረናል” ያሉት ምክትል አፈ-ጉባኤዋ "ያለፉ ስህተቶችን ለማረም እንጂ ለትውልድ ለማስተላለፍ አንሰራም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አሁንም የአገሪቱ ጠላት ድህነት እና ኋላቀርነት መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ ዓለምነሽ፣ ህብረተሰቡ የጥፋት ኃይሎችን ከመታገል ባለፈ ሀብትና ጊዜውን በአገሪቱ ድህነትን ለመቀነስ ለሚደረገው ትግል እንዲያውል ጠይቀዋል፡፡
በተለይ ውሱን የአገሪቱን ሀብት ከብክነት እና ጥቂቶች ያለአግባብ ከበለጸጉበት ሙስና ለመከላከል በዋናነት የህብረተሰቡ የቤት ሥራ መሆኑንም አፈ ጉባኤዋ አስረድተዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ በበኩላቸው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በህገ-መንግስቱ ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ሕብረብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
በዓሉ የመደመር እሳቤ እና የብልጽግና ጉዞ በልማት ድሎች ታጅቦ እንዲቀጥልና የኢትዮጵያ ህዳሴ በጽኑ መሠረት ላይ እንዲቆም ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
"ከዚህ ቀደም የፈጸምናቸው ስህተቶች ከማረም ጎን ለጎን ዳግመኛ እንዳይከሰቱ በጋራ መረባረብ ይገባል" ብለዋል ።
“ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር ሆና መቀጠል የምትችለው ዜጎች ተነጣጥለውና የራስን አጥር ሠርተው በመቀመጥ ሳይሆን ድልድይ ገንብቶ በመተባበር ነው” ሲሉም አስረድተዋል፡፡
አቶ አድጎ እንዳሉት አሁን አገሪቱ እየተከተለች ያለው አካሄድ እንደከዚህ ቀደሙ አንዱን ባለቤት ሌላውን ደባል ማድረግ ሳይሆን ሁሉን ተሳታፊ የሚያደርግ ነው።
"በቀጣይ ህገ-መንግስቱን እና የፌደራል ስርዓቱን ከስም ባለፈ በአግባቡ ለመተግበር ብዙ መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡
ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አሠፋ ሃብቶ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም የተከበሩ የብሔር ብሔረሰቦች በዓላት በእውነተኛ እኩልነት ላይ የተመሰረቱ እንዳልነበር አስታውሰዋል፡፡
"የዘንድሮ በዓል በእውነተኛ መከባከር ላይ ተመስርቶ በአንድነት እና በመደመር እሳቤ ማክበራችን ልዩ ያደርገዋል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በበዓሉ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ጭፈራቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል።
የክልሉ ፖሊስ ማርሽ ባንድ ቡድን የተያዩ ጥኡመ ዜማዎችን ያቀረበ ሲሆን ወታደራዊ ትርኢቶችና ሌሎችም ዝግጅቶች ቀርበዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡