ቀጥታ፡

በኢትዮጵያችን ሕልውና ሳንደራደር የጋራ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ መስራት አለብን -ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ህዳር 29/2012 በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ሳንደራደር የጋራ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ መስራት አለብን ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ ። ፕሬዚዳንቷ ይህን ያሉት 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲከበር ነው። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ተባብረን፣ ተደጋግፈንና ተደማምጠን ብቸኛ የጋራ ቤታችንን ለመገንባት በጋራ መስራት አለብን ብለዋል። በጎደለው ላይ በማላዘን ብቻ ሳይሆን ችግሮችንም በጋራ በመፍታት በኢትዮጵያችን ህልውና ላይ ሳንደራድር የነገን ተስፋ ብሩህ ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያሉት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቷ የገጠማትን ችግር ለመሻገርም በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ ብሔራዊ መግባባትና አንድነት እንዲበለጽግ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ዜጎች ሊገነዘቡት የሚገባው የሌላውን መብት ማክበር የራስንም መብት ማስከበር መሆኑን በማመን መተግበር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። "የአንዳችን ጥቅም የሁላችንም ትንሳኤ፤ የሌላችን ጉድለት የሁላችንም ኪሳራ አድርጎ የሚወስድ ዜጋ  መፍጠር መቻል አለብን" ብለዋል። ሁላችንም ዜጎች በአገራችን ጉዳይ እኩል ተሳታፊ መሆን አለብን የሚለው ቁልፍ መርህ በተግባር መረጋገጥ እንዳለበትም ተናግረዋል። ዜጎች ለአገራቸው ያላቸው ፍቅር እየጎለበተ በሄደ ቁጥር ሠላም ያብባል፣ የኢኮኖሚ አቅም ይፈረጥማል፣ ማህበራዊ መስተጋብሯ ከግጭትና የእርስ በእርስ ጸብ ይርቃል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ። ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ ባህሎቻችንና እሴቶቻችን የበለጠ እንዲጎለብቱ አንድነቱን ማጠናከር አለበት ሲሉ አሳስበዋል። ሁሉም የሚያምረው፣ እንደ ሰውም የምንኖረው ኢትዮጵያ ስትኖር በመሆኑ በኢትዮጵያችን ሕልውና ሳንደራደር የጋራ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ መስራት አለብን ብለዋል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም