ውህደቱ ተጨናግፎ የነበረውን የኢህዴን የቀድሞ ራእይ የሚያሳካ ነው ... የቀድሞ የኢህዴን ታጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
ውህደቱ ተጨናግፎ የነበረውን የኢህዴን የቀድሞ ራእይ የሚያሳካ ነው ... የቀድሞ የኢህዴን ታጋዮች
ኢዜአ ህዳር 29 2012 ..የብልጽግና ፓርቲ በውህደት መመስረቱ ተጨናግፎ የነበረውን የኢህዴንን የቀድሞ ራዕይ የሚያሳካ ነው ሲሉ በዋግ ህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የሚገኙ የቀድሞ የኢህዴን ታጋዮች ገለጹ፡፡ በትግል ስማቸው ጌታሁን አገው በመባል የሚታወቁት ታጋይ ጌታሁን ቸኮል ለኢዜአ እንዳሉት ኢህዴን ህብረ ብሄራዊ እና ሁሉንም ብሄሮች አቅፎ አምባገነኑን የደርግን ስርአት ለመገርሰስ የታገለ ድርጅት እንደነበር አውስተዋል። የኢህዴን ፕሮግራምና ዓላማ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በእኩልነት መብታቸው ተክብሮ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚኖሩበት መሆኑን በመቀበል በ1974 ዓ.ም ወደ ትግሉ መቀላቀላቸውን ያስታውሳሉ ። ይሁን እንጂ ኢህአዴግ በግንባርነት ሃገሪቱን ባስተዳደረባቸው ከሁለት አስር ዓመታት በላይ ብሄርተኝነትን ትኩረት አድርጎ በመስራቱ የሃገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ እንዲወድቅ እንዳደረገው ታጋይ ጌታሁን ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በውህደት የብልጽግና ፓርቲን መመስረታቸው የቀድሞው የኢህዴን ራዕይ የሆነውን ህብረ ብሄራዊ አንድነት በማስፈን ብሄር ብሄረሰቦች በሃገሪቱ ጉዳይ ላይ እኩል ተሳታፊ የሚሆኑበትን እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል። እንደ ታጋይ ጌታሁን ገለጻ አንዱ ብሄር የበላይ ሌላኛው የበታች የሚሆንበት አደረጃጀትና አሰራር በአዲሱ የብልጽግና ፓርቲ እንደማይኖር ያላቸውን እምነት አስቀምጠዋል። በአዲሱን ውህድ ፓርቲ አላማና ፕሮግራም ዙሪያ የሚነዙ አሉባልታዎችን ለማክሰም ለታችኛው ማህበረሰብ ስለ አዲሱ ፓርቲ ተከታታይ ግንዛቤ ማስረፅ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ታጋይ ኮማንደር ወሰን መኳንት በበኩላቸው ብልፅግና ፓርቲ ማንኛውም የሃገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሃገሪቱ ጉዳይ ላይ የመወሰን ስልጣን እንደሚያጎናፅፈው ተናግረዋል ። ኢህዴን ለሁሉንም ብሄር ብሄረሰብ ህዝቦች እኩልነትና ለሃገሪቱ ነጻነት እንዳታገለ ያወሱት ኮማንደር ወሰን ውህድ ፓርቲው መስመሩንና ርዕዮተ ዓለሙን በማጥራት የሃገሪቱን የመከፋፈልና የመበታተን አደጋ መታደግ አለበት ብለዋል ። ሌላው የቀድሞ ታጋይ ወንድማገኝ ማሞ በበኩሉ አሁን የተመሰረተው ብልፅግና ፓርቲ ብሄር ብሄረሰቦች በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል የሚል እምነት አላቸው። ኢህዴን ወደ ግንባር በተቀላቀለባቸው 28 ዓመታት በሃገሪቱ የልማት እምርታዎች ያስመዘገበ ቢሆንም የብሄር አክራሪነትና ኢፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጎልቶ መታየቱን ተናግረዋል። ይህም በሂደት ህዝባዊ ቅራኔ በመፍጠሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲከሰት በማድረግ ለዜጎች ሞት፣ አካል መጉደልና ንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል። ‘’አሁን ላይ የአጋር ድርጅቶችን በማቀፍ ወደ ውህድ ፓርቲ መሸጋገር መቻሉ ደግሞ ተገቢና ወቅቱ በሚፈልገው መልኩ ብሄር ብሄረሰቦችን እኩል የሚያሳትፍ ነው ‘’ሲሉ ታጋይ ወንድማገኝ ገልጸዋል። በቀጣይም ውህድ ፓርቲው የውስጠ ድርጅት ስራውን በማስተካከል የሃገሪቱን መጻኢ ጊዜ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እድገትን ማፋጠን ይኖርበታል ብለዋል፡፡ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የተክለ ኢህዴን የቀድሞ ታጋዮች ራስ አገዝ ማህበር አስተባባሪ ታጋይ ሰለሞን መሃመድ በበኩላቸው በ1975 ዓ.ም የኢህዴንን አላማ እና ፕሮግራም ተቀብለው ወደ ትግል እንደተቀላቀሉ ተናግረዋል፡፡ የፖለቲካ ቀውሶችን ለመቅረፍ በውህደት የብልጽግና ፓርቲን መቋቋሙ አገራችን አሁን የገጠማትን ችግር ለመቅረፍ መሰረት መሆኑን ታጋይ ሰለሞን ገልፀዋል ። የብልጽግና ፓርቲ በቀጣይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ያጋጠመንን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውሶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ሰላምና መረጋጋት ማስፈን እንዳለበት ጠቅሰዋል። ለዚህም ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች አካላት ከራስ ጥቅም ይልቅ የሃገርን እና የህዝብን ህልውና በማስቀደም ከፓርቲው ጎን እንዲቆሙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።