ፌዴራላዊ ስርዓቱ በወንድማማችነት ጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆምና ሁሉንም ተጠቃሚ እንዲያደርግ መትጋት ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴራላዊ ስርዓቱ በወንድማማችነት ጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆምና ሁሉንም ተጠቃሚ እንዲያደርግ መትጋት ያስፈልጋል
ህዳር 29/2012 ፌዴራላዊ ስርዓቱ በወንድማማችነት ጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆምና ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ እንዲያደርግ መትጋት እንደሚያስፈልግ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ። 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በአዲስ አበባ የተከበረ ነው። በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ቀኑ ኢትዮጵያዊያን ሁለንታናዊ መብታቸው በሕገ-መንግስት የተደገፈበት ዕለት ነው ብለዋል። ቀኑ ሲታሰብ የኢትዮጵያ ብሔሮች ሰብዓዊ መብታቸውን ጨምሮ የአስተዳደራዊ መብታቸውን በራሳቸው መወሰን የቻሉበትም ነው ብለዋል። "ይህ እንዲሆን ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል" ያሉት አቶ ሽመልስ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ ሆነው እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን መፍታት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ አንዱ ታዛዥ ሌላው አዛዥ፣ አንዱ በይ ሌላው ተመልካች፣ በጥቅሉ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የማይሆንባትና እኩልነት የነገሰባት ትሆናለች ብለዋል። ይህ የሚሆነው ደግሞ የተጀመረው ፌዴራላዊ ስርዓት በወንድማማችነት ጽኑ መሰረት ላይ ሲቆም መሆኑን በመረዳት መትጋት ያስፈልጋል ነው ያሉት አቶ ሽመልስ። "ይህ ሲሆን ኢትዮጵያ ያለ ስጋት ጠንካራ አገር ሆና ትቀጥላለች" ያሉት አቶ ሽመልስ ኢትዮጵያዊ ማንነት የብሔሮች ማንነት ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል። አቶ ሽመልስ ቀድሞም ችግር ፈጣሪዎች የነበሩ አካላት ዛሬ ችግር ፈቺ ሆነው መቅረባቸው ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።