የግል ባንኮችን ጮቤ ያስረገጠው የመንግስት ውሳኔ አንድምታ

67

በሀብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ)

ሰሞኑን በኢትዮዽያ የግል ባንኮች የቢዝነስ ኢንዱስትሪ ውስጥ አንድ መልካም ዜና ተሰምቷል። ዜናው ባለፉት ስምንት አመታት ገደማ የግል ባንኮቹ ተደጋጋሚ ቅሬታን ሲያቀርቡበት የነበረ ጉዳይ እልባት ማግኘትን አብስሯል። ይኸውም የግል ባንኮቹ ከሚሰጡት ብድር ላይ 27 በመቶውን ስሌት ውስጥ በማስገባት ለቦንድ ግዢ እንዲያውሉ የሚያስገድዳቸው መመሪያ ነበር። ይህ መመሪያ ነው እንግዲህ በብሄራዊ ባንክ መሻሩ የተነገረው፤ የግል ባንኮቹ እስካሁን በ27 በመቶ አስልተው ከ116 ቢሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዢ መፈፀማቸውም ተገልጿል። አስገዳጅ መመሪያውን 16 የግል ባንኮች ተግባራዊ ሲያደርጉ መቆየታቸው የተነገረ ሲሆን፤ ባንኮቹ ለፈፀሙት የቦንድ ግዢ የመክፈያ ጊዜ ደርሶ የተከፈላቸው 30 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደሆነም ተገልጿል።

የብሄራዊ ባንክ ዋና ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በብሄራዊ ባንክ ሃላፊነት ላይ ከተቀመጡ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ከባንከ ባለሙያዎች ጋር አድርገውት በነበረው ስብሰባ ላይ አስገዳጅ መመሪያው ሊነሳ እንደሚችል ቃል ገብተው እንደነበርም የሚዘነጋ አይደለም። በወቅቱም የግል ባንኮቹ ሃላፊዎች ከመመሪያው አንፃር በርካታ አሉታዊ ሃሳብ ማንፀባረቃቸውም እንደዛው፤ በዚህ ወቅት ነበር የብሄራዊ ባንክ ገዢው መንግስት መመሪያውን ለማንሳት ስትራቴጂዎችን እየቀየሰ እንደሆነ የተናገሩት። በቃላቸውም መሰረት ህዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም አስገዳጅ መመሪያው እንዲነሳ ተደርጓል። በግል ባንኮቹም ዘንድ ውሳኔው ከፍተኛ ደስታን የፈጠረ እንደሆነ እየተገለፀ ይገኛል።

ለመሆኑ አስገዳጅ መመሪያው መነሳቱ በኢንዱስትሪውም ሆነ በአጠቃላይ የሃገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚኖረው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን የምንጠብቀው ጥያቄ ነው። ባንኮቹ መመሪያ ከመነሳቱ በፊት ገቢ ያደርጉት የነበረው የገንዘብ መጠን በባንኮቹ አማካይነት ወደ ስራ ሲገባ የሚኖረው ተፅዕኖን እንዴት ለመቋቋም ታስቧል የሚሉት ሃሳቦች በዘርፉ ባለሙያዎች እንዴት ይታያሉ? የግል ባንኮቹ ሃላፊዎችም ሆኑ ሌሎች የፋይናንስ ባለሙያዎች በዚሁ ረገድ የተለያዩ ሃሳቦችን አንፀባርቀዋል። አንዳንድ የግል ባንከ ሃላፊዎች መመሪያው ተግባራዊ የተደረገው ሆን ተብሎ የግል ባንኮችን ለማዳከም ነው ብለው ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ መመሪያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንዲሁም የኢትዮጵያ ልማት ባንክን የማይመለከት ሆኖ መሰራቱ ቀደም ብሎ የተጠቀሰውን ሃሳብ እንደሚያጠናክረው ይጠቅሳሉ።

የሆነው ሆኖ ግን አብዛኞቹ የባንክ ሃላፊዎችም ሆኑ የፋይናንስ ባለሙያዎች አስገዳጅ ህጉ መነሳቱ ለግል ባንኮቹ የብድር አቅርቦት ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ አንስተዋል። አስገዳጅ መመሪያው አይ ኤም ኤፍን በመሰሉ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ዘንድም ትችት ሲሰነዘርበት ከርሟል።መመሪያው የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እንዲገጥመው አድርጓል የሚል ሃሳብን አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አንፀባርቋል። በኢትዮጵያ የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ቋሚ ተወካይ ጁለስ ሌይቺተር ከካፒታል ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ የብሄራዊ ባንክ ውሳኔ አዎንታዊ እንደሆነና ተቋማቸውም መሰል ተግባርን እንደሚደግፍ አንስተዋል። እንደ እሳቸው የመመሪያው መነሳት የግል ባንኮቹን የማበደር አቅም በመጨመር የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚን ከማሳደግ አንፃር ሚናው የጎላ ነው።

በመንግስታቱ ድርጅት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት እዮብ ተስፋዬ በበኩላቸው በአስገዳጅ መመሪያው መነሳት የተገኘው ፋታ ለባንኮቹ እጅግ አስፈላጊና በብድር አቅርቦት ማነስ አላስፈላጊ ፉክክር ውስጥ ገብተው ሲዳክሩ ለነበሩ የግል የፋይናንስ ተቋማት የማበደር አቅም እንደሚፈጥርላቸው ይናገራሉ። ልክ እንደ አይ ኤም ኤፍ ሃላፊው ሁሉ አቶ እዮብም የግል ባንኮቹ የማበደር አቅም ማደግ የሃገሪቷ ምጣኔ ሃብት ሞተር የሆነውን የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እንደሚያሳድገው ይስማማሉ። የመመሪያው መነሳት ያልተጠበቀና ለፋይናስ ዘርፉ ትልቅና አስደሳች ዜና እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጄ ዘነበ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት መመሪያው የባንኮችን የማበደር አቅም ከመፈተኑም በላይ ባንኮቹ የብድር የወለድ መጠንን እንዲጨምሩ አድርጓል። ባንኮቹ የወለድ መጠንን ሲጨምሩ ደግሞ ሌሎች የስራ መስኮች ለጉዳት እንደተጋለጡ አንስተዋል።  እንደ አቶ ደረጄ ሃሳብ የአስገዳጅ መመሪያው መነሳት በባንኮቹ ላይ የነበረውን ጫና ብቻ ሳይሆን በተበዳሪዎች ላይ የነበረውንም አስፈላጊውን ብድር የማግኘት እክል ሊቀርፍ ይችላል።

በአንፃሩ መንግስት አስገዳጅ መመሪያውን ማንሳቱ የራሱ የሆኑ አሉታዊ ጎኖች አሉት ያሉት የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያዎቹ፤ መንግስት ከሚመጣው ተፅዕኖ ሊያላቅቀው የሚችልባቸውን መፍተሄዎች ሊያበጅ እንደሚገባም ይመክራሉ። አንዳዶች ባለሙያዎች እንዳሉት የ27 በመቶ አስገዳጅ መመሪያ መነሳት በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ በአሰከፊ ሁኔታ እየተስተዋለ ያለውን ግሽበት ሊያባብሰው እንደሚችል ነው። የአስገዳጅ መመሪያው መውጣት ዋነኛ ምክንያት የነበረው የዋጋ ግሽበትን መከላከል እንደነበር ያስታወሱት አቶ እዮብ ማዕከላዊ ባንኩ ገንዘብን በሌላ አቅጣጫ እንዲወጣ በማድረጉ መመሪያው ፍሬያማ ሊሆን እንዳልቻለ አንስተዋል።  የመመሪያው መነሳት ግሽበትን እንደሚያባብስ አድርጎ ብቻ ማሰብም አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ነው አቶ እዮብ የሚያነሱት። የአለም ባንክ ቋሚ ተወካዩ ጁለስ ሌይቺተር በበኩላቸው ባንኮቹ የ27 በመቶው ስሌት እንዲቀርላቸው በመደረጉ የገንዘብ አስተዳደር ማዕቀፍ ፖሊሲዎቻችውን በማዘመን ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አስረድተዋል። በእሳቸው እምነትም መንግስት የተለየ ዘዴ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ነው። ይሀውም መንግስት ባንኮቹ የቻሉትን ያህል የቁጠባ መጠናቸውን እንዲጨምሩና በቁጠባ የሰበሰቡትን ገንዘብ ለግል ባለሃብቶች በብድር መልክ ማቅረብ ሊሆን እንደሚችል ነው። ለዚህም ይመስላል መንግስት ከዚህ ቀደም አቋርጦት የነበረውን የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ መጀመሩን ሰሞኑን ከዜና ማሰራጫዎች መስማታችን። ከዚህም በዘለለ መንግስት የሞኒተሪ ፖሊሲውን ማጠናከር እንደሚገባው  ነው ሁኔታዎች የሚያሳዩት።

መንግስት አስገዳጅ መመሪያውን ተግባራዊ እንዲያደርግ ካስገደዱት ጉዳዮች አንዱ የግል ባንኮቹ የረጅም ጊዜ ብድር መስጠት ላይ የሚያሳዩትን የተነሳሽነት ማነስ ለማካካስ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ። ማኑፋችተሪንግ እና አግሮ ፕሮሰሲንግን የመሳሰሉ የቢዝነስ ዘርፎች የረጅም ጊዜ ብድርን የሚፈልጉ ሲሆን፤ የግል ባንኮቹ ደግሞ በረጅም ጊዜ ውስጥ ለሚመለስ የብድር አይነት ገንዘባቸውን ለማበደር ፈቃደኞች አይደሉም ይላሉ ባለሙያዎቹ። በተጨማሪም ባንኮቹ ሰፋ ያለ ብድርን የማቅረብ የአቅም ውስንነት አለባቸው። በተቃራኒውም የግል ባንኮቹ የንግድ እስከመሆናቸው ድረስ በሚያዋጣቸው እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመላሽ ሊሆን በሚችል የብድር አቅርቦት ላይ መሰማራታቸው ከሃጢያት ሊቆጠርባቸው እንደማይገባም ይከራከራሉ።

የሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ይፋ በተደረገበት ወቅት መንግስት የተለያዩ ልማቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ የፋይናንስ የአሰራር ዘዴዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እንዳሰበ መግለፁም ይታወሳል። መንግስት የሚበደረውን ገንዘብ በመቀነስ የገንዘብ አቅርቦቱን ብሎም ግሽበቱን መቆጣጠር እንደሚገባው የፋይናንስ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።

መንግስት ሃገሪቱ አሁን ያላትን የንግድ ስራ ምቹነት መመዘኛን ከ50 በላይ ደረጃዎችን የማሻሻል ዕቅድ እንዳላት በቅርቡ መገለፁም ይታወሳል። በዚህም የአለም ባንክ ግሩፕ ከ190 ያላነሱ ሃገራትን የንግድ ስራ ምቹነት ለመመዘን በቅርቡ ይፋ የተደረገው “ኢዝ ኦፍ ዱዊንግ ቢዝነስ 2020” ኢትዮዽያን 159ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። መንግስት የተጠቀሰውን ቁጥር በማሻሻል በሶስት አመታት ውስጥ ሃገሪቷን መቶዎቹ ውስጥ ለማስገባት ዕቅድን ይዟል። መሰል ውጥኖች ወደ ተግባር እንዲለወጡ ደግሞ መንግስት የግሉን ዘርፍ ማበረታታት ቀዳሚ ስራው ሊያደርገው ይገባል። ለዚህም ይመስላል በግል ንግድ ባንኮች ላይ ተጥሎ የነበረውን አስገዳጅ መመሪያ በማያወላዳ መልኩ እንዲነሳ ማድረጉ፤ ይበል የሚያሰኝ ታላቅ እርምጃ ነው እንላለን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም