ቀጥታ፡

ህዳር 29 የኢህአዴግ ስጦታ ተደርጎ መቅረቡ ፖለቲካዊ ኪሳራን አስከትሏል ... ምሁራን

ኢዜአ፤ ህዳር 28/2012 ኢህአዴግ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት  ለፖለቲካዊ ትርፍ በማዋሉ ህዳር 29  የህብረ-ብሄራዊ ማሳያ ከመሆን ይልቅ የመፎካከሪያ መድረክ ሆኖ መቆየቱን ምሁራን ገለጹ ፡፡

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የህግ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ እንዳሉት የኢትዮጵያ ታሪክ የህዝቦች የንግድ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የጋብቻ ና የማህበራዊ ኑሮ የተጠናከረ ነበር።

ይሁን እንጂ የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ፖለቲከኞች የህዝቦችን ግንኙነት በማሻከር የሀገር ግንባታ ሂደቱን እየጎተቱ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ከጸደቀበት ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ ፌደራላዊ ስርዓት መኖሩ ቢነገርም ከአፍአዊነት በዘለለ ገቢራዊ ባለመሆናቸው የብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደርና ሌሎች ጥያቄዎች እስካሁን ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡

ህዝቦች አንድነታቸውን አጠናክረው የሀገር ግንባታን እውን ለማድረግ የፌደራሊዝም ስርዓት ትልቅ ሚና አለው ያሉት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር አንተነህ ገዛኸኝ፤ ህገመንግሥቱ የጸደቀበትን ዕለት ለማክበር በየዓመቱ በሚሰናዳው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ላይ ልዩነት ጎልቶ አንድነት ተረስቶ ስንጓዝ ነበር” ብለዋል።

በዓሉ የከረሩ የፖለቲካ የልዩነት አቋሞች ባሉባት ሀገር ልዩነትን ለማጥበብና አንድነትን ለማጠናከር ፋይዳው የላቀ ቢሆንም በተግባር ግን የሚጠበቅበትን ውጤት አላስገኘም በማለትም መምህር አንተነህ ይገልጻሉ።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል መኮንን በበኩላቸው፤ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓትን መከተል የጀመረችበትን ቀን የሚዘክር  ቢሆንም፤ ባለፉት ዓመታት ለፖለቲካዊ ዓላማ ብቻ መዋሉንም ጠቅሰዋል።

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንዳሉት “ህዳር 29 ላለፉት ከ20 በላይ ዓመታት የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ስጦታ ተደርጎ ነው የታየው፤ ብዙ ሰዎች የኢህአዴግ ቀን አድርገው ነው የሚወስዱት፤ ቀኑን ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ባያደርገው መልካም ነበር።”

“ከፖለቲካ ነጻ ቢደረግ ኖሮ በእኩልነት የሁሉም ህዝቦች ቀን ብለን እናከብረው ነበር፤ ኢህአዴግ በሰራው ስህተት ግን መፈራረጃ ሆኗል” ይላሉ።

በተለያዩ ሀገራት ህዝቦችን ወደ ብሔራዊ አንድነት ከሚያመጡ ጉዳዮች ክብረበዓል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያም የአድዋ ድል በዓል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአንድነት ምልክት እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን በብሔር ብሔረሰቦች ቀን የአያቶቻቸውን ጀግንነትና የጋራ የቀድሞ የስልጣኔ እሴቶቻቸውን በማውሳት፤ አሁን ላለው የሀገር ግንባታ የሚያውሉበት ስልት እንዲተገበር  የጠየቁት የህግ መምህር አንተነህ፤  ህዝቦች ባህልና ሃይማኖታቸውን መሰረት ያደረጉ በዓላትን አንዱ የሌላውን በጋራ እያከበሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ህገመንግሥቱ የጸደቀበትን ዕለት ለማስታወስ  የብሄረሰቦች በዓል ለይስሙላ ሲከበር መቆየቱን የተናገሩት ዶክተር አልማው፤ “የለውጥ ሃይሉ” ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ለእውነተኛ የፌደራሊዝምና ለህብረ ብሔራዊት ሀገር ግንባታ በር መከፈቱን ነው የገለጹት።

ባለፉት ከ25 ዓመታት በላይ የህዝቦች አብሮ የመኖር እሴት እንዲጠፋና በኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ ያለውን ማህብረሰብ በፖለቲካ ልዩነት እርስ በእርስ እንዲጋጩ መሰራቱን ነው የጠቀሱት።

ፖለቲኮኞችም አንዱን ብሔር ተጨቋኝ፤ ሌላውን ደግሞ ጨቋኝ አድርጎ በማንሳት ህዝቦችን ለማራራቅ የሰሩት ስህተት ለሀገር ግንባታ ሂደት ፈታኝ በመሆኑ፤ ዘንድሮ በሚከበረው የህዝቦች ቀን የአንድነት እሴቶች እንዲንጸባረቅበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የተለያየ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት ያላቸው ህዝቦች በአድዋ በአንድነት ጠላትን በመመከት አኩሪ ታሪክ መስራታቸው ጠቅሰው፤ አሁን የተጀመረው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና  ማህበራዊ ጥያቄዎችን የመመለስ ሂደት እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።

“የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በሀገራችሁ ጉዳይ አያገባችሁም ተብለው ተገልለው የነበሩ በሀገራቸው ጉዳይ መሳተፍ በጀመሩበት፣ ብቃት ቢኖራቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የማይችሉ የነበሩ ወደሚሆኑበት በተሸጋገሩበት ጊዜ ላይ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል” ብለዋል።

“ድጋፍና ተቃውሞን የሚያስተናግደው ህገ መንግሥት ልደቱ በሚከበርበት ህዳር 29 ቀን በልሂቃን መካከል ያሉትን ልዩነቶች ለማጥበብ፣ ህዝቦች በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በአንድነት እንዲሰለፉ መጠቀም አለብን” ያሉት ደግሞ ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ናቸው።

የብሄር ብሔረሰቦች ቀንን ከፖለቲካ በላይ ማሰብ ያስፈልጋል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤  በዓሉ የህብረ ብሔራዊነት ማጠናከሪያ ቀን ሆኖ እንዲከበር ነው የጠየቁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም