ቀጥታ፡

አዳዲስ ዝርያዎች ምርታማነታቸውን ከእጥፍ በላይ እንዳሳደጉላቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ

ኢዜአ ህዳር 28 ቀን 2012 ከሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል የሚወጡ የተሻሻሉ የሰብልና የጥራጥሬ ዝርያዎች መጠቀማቸው ምርታማነታቸውን ከእጥፍ በላይ እንዳሳደገላቸው በባሌ ዞን የአጋርፋና ሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡ የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በበኩሉ የአርሶ አደሩን ምርታማነትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የጥራጥሬና የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከማዕከሉ በምርምር የወጡ የሰብል ዝርያዎችን በማህበር ተደራጅተው በማባዛት ውጤታማ የሆኑ የአጋርፋና ሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች ማሳ ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በተጋበዙ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ተጎብኝቷል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች እንዳሉት ምርታማነታቸው ያደገው በሽታን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን ዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችን ተጠቅመው በማልማታቸው ነው።

የሰልቃ ቀበሌው አርሶ አደር የባ መሐመድ ቀደም ሲል ከአንድ ሄክታር የአካባቢ (የስንዴ) ዝርያ የሚያገኙት ምርት ከ15 ኩንታል ይበልጥ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ከማዕከሉ ያገኙትን ምርጥ የስንዴ ዝርያ ሙሉ የግብርና ፓኬጆችን ተጠቅመው በማልማታቸው በሄክታር ከ70 እስከ 80 ኩንታል በማምረት በሕይወታቸው ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሙሉ የግብርና ፓኬጅ ተጠቅመው በየጊዜው ከሚያመርቱት ምርት ሽያጭ ገቢም በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የህዝብ ማመላለሻ አይሱዙ መኪና መግዛታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በ2011/2012 የመኽር ምርት ወቅት ከሌሎች የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመሆኑ በ13 ሄክታር መሬት ላይ በክላስተር ካለሙት ስንዴ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም አቶ የባ ተናግረዋል፡፡

"ማዕከሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በቅርበት እንዳገኝ ከማድረግ ባሻገር ምርታማነትን ከሚጨምሩ የግብርና አሰራሮች ጋር እንድተዋወቅ ረድቶኛል" ያሉት ደግሞ የአጋርፋ ወረዳ አሊ ቀበሌ አርሶ አደር አህመድ ጠይብ  ናቸው ።

”ከሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ያገኘሁትን የተሻሻለ የስንዴ ዝርያ በማልማት በሄክታር አገኝ የነበረውን 15 ኩንታል ወደ 65 ኩንታል ማሳደግ ችያለሁ” ብለዋል ፡፡

በመኽር ምርት ወቅት በስድስት ሄክታር መሬት ላይ ከሌሎች የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመደራጀት በኩታ ገጠም የግብርና አሰራር ዘዴ ያለሙት ስንዴ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝና የተሸላ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡

ሌሎች አርሶ አደሮችም ከማዕከሉ የሚለቀቁ ዝርያዎችን ከመጠቀም ባለፈ የግብር ባለሙያዎችን ምክር ቢተገብሩ ምርታማ እንደሚሆኑ አርሶ አደሩ ገልጸዋል።

የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ በሪሶ በበኩላቸው እንዳሉት ማዕከሉ የአርሶ አደሩን ምርታማነትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የጥራጥሬና የሰብል ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚው ለማድረስ እየሰራ ነው፡፡

"ማዕከሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በምርምር ከማፍለቅ በተጓዳኝ ውጤቱ ለተጠቃሚው አርሶ አደርና ሌሎች በግብርና ኢንቨስትመንት ሥራ ለተሰማሩ ባለሀብቶች እንዲደርስ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኘል" ብለዋል፡፡

በ2011/2012 የመኽር ወቅት ከግብርና እድገት ፕሮግራም ጋር በመተባባር በዞኑ የአጋርፋና ሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር ተጠቅመው በ250 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም እንዲያለሙ መደረጉን ለእዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ እና የኦሮሚያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አማካሪ ዶክተር አበራ ዴሬሳ በበኩላቸው መንግስት የአርሶ አደሩ ምርታማነት በመጨመር ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

"ለእዚህም17 የግብርና ምርምር መዕከላትን አቋቁሞ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማላማድ አርሶ አደሩን እየደገፉ ይገኛሉ" ብለዋል፡፡

በባሌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ከሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ከዚህ በፊት የተለቀቁ የስንዴ ዝርያዎችን በክላስተር በማልማት ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮችም የዚሁ ጥረት አካል መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

አዳዲስ ዝርያዎችን ማፍለቅ ብቻውን ግብ ዓለመሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አበራ፣ በአገሪቱ ከሚገኙ የግብርና ምርምር ማዕከላት የሚወጡ የተለያዩ ትክኖሎጂዎች ተጠቃሚው ዘንድ ደርሰው ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በ1978 ከተቋቋመ ወዲህ 78 በምግብ እህል፣ በጥራጥሬና በእንስሳት መኖ ላይ ያተኮሩ የምርምርው ጤቶችን ለተጠቃሚው ማድረሱ ተመልክቷል፡፡

በባሌ ዞን የአጋርፋና ሲናና ወረዳዎች ውስጥ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የመስክ ቀን ጉብኝት ላይ ከኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት የተጋበዙ እንግዶችን ጨምሮ ከባሌና ምዕራብ አርሲ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም