ይድነቃቸው ተሰማ በኮከቦች ሽልማት የሕይወት ዘመን ተሻላሚ በመሆን ታወሱ

ኢዜአ ህዳር 28 ቀን 2012 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2011 ዓ.ም የኮከቦች ሽልማት አቶ ይድነቃቸው ተሰማን የሕይወት ዘመን ተሸላሚ በማድረግ አስታውሷቸዋል።

የፋሲል ከነማው ሱራፌል ዳኛቸው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ የአዳማ ከተማዋ ሴናፍ ዋቁማ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ተሸላሚ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2011 ዓ.ም የኮከቦች ሸልማት ትናንት ምሽት ተካሄዷል።

የ2011 ዓ.ም ኮከቦች ሽልማት የተበረከተው ፌዴሬሽኑ ባካሄዳቸው ስድስት ውድድሮች የተሻለ ብቃት ላሳዩ ስፖርተኞች ነው።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ፣ የአንደኛ ሊግ፣ በሴቶች ፕሪሚየር አንደኛና ሁለተኛ ዲቪዚዮን የ20 በታች የፕሪሚየር ሊግ ፌዴሬሽኑ ያካሄዳቸው ውድድሮች ናቸው።

በተጨማሪም የሕይወት ዘመን ተሸላሚ እና የዓመቱ ልዩ ተሸላሚ ሽልማቶች ተበርክተዋል።

አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ህዳር 13 ቀን 1979 ዓ.ም ሕይወታቸው እስካለፈ ጊዜ ድረስ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የስፖርት ሰው ነበሩ።

የአፍሪካ እግር ኳስ አባት በመባል የሚታወቁት ይድነቃቸው ተሰማ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሕይወት ዘመን ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል።

ከሕልፈታቸው 33 ዓመት በኋላ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የህይወት ዘመን ተሸላሚ ሲል አቶ ይድነቃቸውን አስታውሷቸዋል።

ከአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸው ሽልማቱን ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ እና ከስፖርት ኮሚሽነሩ ኤልያስ ሽኩር ተቀብለዋል።

አቶ ታደለ ፌዴሬሽኑ አቶ ይድነቃቸው ተሰማን በማስታወስ ላበረከተው ሽልማት አመስግነው ለቤተሰባቸው ትልቅ ደስታ እንደሆነ ገልጸዋል።

አባታቸው 'ከምንም በላይ ዝናን ማግኘት ሳይሆን ዝናን አስጠብቆ መኖር ወሳኝ ነው' ይሉ እንደነበረ ያስታወሱት አቶ ታደለ ስፖርተኞች ዝና ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ከዝና ጋር ለመኖር መትጋት አለባቸው ብለዋል።

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማና ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ኢትዮጵያን በአፍሪካ መድረክ በማስጠራት ላሳዩት ድንቅ ብቃት የፌዴሬሽኑ ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል።

በተጨማሪም ከ30 ዓመት በላይ በእግር ኳስ ሜዳዎች ለሚጎዱ ተጫዋቾች ህክምና በመስጠት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱት የኢትዮጵያ ቡና የህክምና ባለሙያ አቶ ይስሀቅ ሽፈራውም ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል።

የፋሲል ከነማው ሱራፌል ዳኛቸው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአዳማ ከተማዋ ሴናፍ ዋቁማ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ኮከብ ተጫዋች ሽልማትን አግኝተዋል።

የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ አሰልጣኝ ሆነዋል።

የሰበታ ከተማው ጌቱ ኃይለማርያም የከፍተኛ ሊግ ኮከብ ተጫዋች ሽልማት ሲያገኝ የኮልፌ ቀራኒዮው ፈቱ አብደላ የአንደኛ ሊግ ኮከብ ተጫዋች ሽልማት ተመረክቶለታል።

የሀዋሳ ከተማው መስፍን ታፈሰ ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማዋ ንግስቴ ኃይሉ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ኮከብ ተጨዋች ሽልማት አግኝተዋል።

በተጨማሪም በስድስቱ ውድድሮች የዓመቱ ምስጉን ዋና ዳኛና ረዳት ዳኛ፣ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ፣ ኮከብ አሰልጣኝና ኮከብ ግብ ጠባቂ ሽልማትና የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት ደግሞ ለክለቦች ተበርክቷል።

ፋሲል ከነማ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ አዳማ ከተማ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት ያገኙ ክለቦች ናችው።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ሽልማቱ በ2011 ዓ.ም ፌዴሬሽኑ ባካሄዳቸው ውድድሮች የተሻለ ብቃት ላሳዩ እውቅናና ማበረታቻ ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑ ገልጸዋል።

እውቅና ከመስጠት ባለፈ ስፖርተኞቹ በቀጣይ ውድድሮች ተግተው በመስራት የተሻለ ውጤት እንዲያሳዩ ኃላፊነት የሚሰጥም ነው ብለዋል።

የኮከቦች ሽልማት ስፖርተኞች በእግር ኳስ ሜዳ ላሳዩት ብቃት ከሚሰጠው እውቅና ባሻገርም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች ክብር የሚሰጥበት እንደሆነም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አቶ ኢሳያስ በተያዘው የውድድር ዓመት ጤናማ የውድድር መድረክ እንዲኖር በእግር ኳሱ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን ስርዓት አልበኝነት ልንዋጋው ይገባል ብለዋል።

ስፖርታዊ ጨዋነትን በእግር ኳስ ሜዳዎች የማስፈን ጉዳይ የፌዴሬሽኑና የጸጥታ አካላት ስራ ብቻ እንዳልሆነና ሁሉም የስፖርቱ አካላት ሃላፊነት እንዳላባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ፣ የስፖርት ኮሚሽነር ኤልያስ ሽኩር እና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተዘጋጁትን ሽልማቶች አበርክተዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ የስራ ክፍል፣ ክለቦችና የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በኮከቦች ሽልማት ድምጽ አሰጣጥ ላይ መሳተፋቸው በሽልማት ስነ ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም