ቀጥታ፡

በባህርዳር ከተማ የሚመረተው ውሃ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ እየዋለ አለመሆኑ ተገለጸ

ኢዜአ ህዳር 28 ቀን 2012 በባህር ዳር ከተማ በውሃ አያያዝና አጠቃቀም ጉድለት በሚፈጠር የውሃ ብክነት ምክንያት ለነዋሪዎች በቂ ውሃ ለማቅረብ መቸገሩን የከተማው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የውሃ ብክነትን ለመቀነስ እንዲቻል ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል። በከተማው 703 ሊትር ውሃ ፐር ሰከንድ እየተመረተ ቢሆንም ለነዋሪዎች ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው 62 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል። የጽህፈት ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም አሰፋ እንዳሉት እየተመረተ ያለውን ውሃ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ተቸግረዋል። “የመብራት መቆራረጥ፣ የፓፕም አቅርቦት እጥረት፣ የውሃ አጠቃቀም ጉድለት፣ የመንገድ ችግር፣ የውሃ መስመር በህገወጦች መቆረጥና ሌሎች ችግሮች ለውሃ ፍትሀዊ አቅርቦት መጓደል ምክንያቶች ናቸው” ብለዋል። የሚመለከታቸው ተቋማት ተቀናጅተው አለመስራት ችግሩን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ እንዳይሆን ማድረጉንም ተናግረዋል። የምክክር መድረኩ ዓላማም በችግሮች ላይ ተወያይቶ የጋራ መግባባት በመፍጠር በቀጣይ ተባብሮ ለመስራትና የውሃ ብክነትን ለማስቀረት መሆኑን የገለጹት አቶ ዘላለም፣ ይህም የከተማው ነዋሪዎች እየገጠማቸው ያለውን የውሃ እጥረት ለመፍታት እንደሚያግዝ አስታውቀዋል። የአማራ ክልል ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ውሃ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው በበኩላቸው በባህር ዳር ከተማ የውሃ አቅርቦትና ፍትሃዊ ስርጭት ችግር መኖሩን ጠቁመዋል። “ችግሩን ለመፍታት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲንና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማትን በማካተት የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ የችግሩን ምንጭ በጥናት የመለየት ስራ ተሰርቷል” ብለዋል። የተመረተውን ውሃ በፍትሃዊናት ያለምንም ብክነት ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ በቅንጅት እንደሚሰራም አመልክተዋል። የውሃ ምንጮችና ጉድጓዶች ባሉባቸው አካባቢ የሚከሰት የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግሮርን ፈጥኖ ለመፍታትይ የመንገድ መሰረተ ልማት አለመኖር እንቅፋት እንደሆነባቸው የተናገሩት ደግሞ በኤሌክትሪክ አገልግሎት የባህር ዳር ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ዘላለም ታደሰ ናቸው። “በቀጣይ የከተማ አስተዳደሩ የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮችን ፈጥኖ ሊፈታ ይገባል” ብለዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የመሰረተ ልማት አማካሪ አቶ ደሳለኝ አስራደ በበኩላቸው የከተሞች ዕድገት እየተፋጠነ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የውሃ አቅርቦትና አጠቃቀም ከዕድገቱ ጋር ሊመጣጠን እንደሚገባ ገልጸዋል። የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የተቀናጀ የመሰረተ ልማት አመራር ተግባራዊ ማድረግና በከተማው ከንቲቫ ሰብሳቢነት ሊመራ እንደሚገባ አመልክተዋል። በባህር ዳር ከተማ 230 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ እንደሚኖር የሚገመት ሲሆን የከተማዋ የመጠጥ ውሃ ሽፋንም 52 በመቶ ላይ መድረሱ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም