በአገሪቱ ሁከትና ብጥብጥን በማስቆም ሰላምን ለማረጋገጥ የዜግነት ፖለቲካ ማራማድ እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በአገሪቱ ሁከትና ብጥብጥን በማስቆም ሰላምን ለማረጋገጥ የዜግነት ፖለቲካ ማራማድ እንደሚገባ ተጠቆመ
ኢዜአ ህዳር 28 /2012 በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚከሰተውን ሁከትና ብጥብጥ በማስቆም ሰላምን ለማረጋገጥ የዜግነት ፖለቲካ ማራማድ ተመራጭ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስታወቀ።
ፓርቲው በወልድያና አካባቢው ለሚገኙ አመራሩና አባላቱ መጪውን ምርጫ አስመልክቶ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥቷል።
የወልድያና የጉባላፍቶ ወረዳዎች ኢዜማ ጽህፈት ቤት ሊቀመንበር አቶ አዳነ ጥላሁን እዳሉት የፖለቲካ ፓርቲ የህዝቦችን ለዘመናት የነበረ አብሮ የመኖር እሴት በማስቀጠል ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር አልሞ መደራጀትና መንቀሳቀስ ይኖርበታል።
በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን ከዚህ በተቃራኒው የህዝቦችን መብትና ፍላጎት ለማፈን ሲውል የሚስተዋልበት ሁኔታ መኖሩንም አስታውሰዋል።
"በአገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የተስተዋለው ሁከትና ብጥብጥ ምንጩ የብሔር ፖለቲካ የወለደው ጽንፈኝነት ነው፤ ይህም በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል" ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ አዳነ እንዳሉት ሕብረተሰቡ በዜግነት ፖለቲካ በመሳተፍ በአገሪቱ አሁን እየታየ ያለውን የብሔር ጽንፈኛነት ከማስወገድ ባለፈ ሁሉም ዜጋ በአገሩ እኩል የመጠቀም እድል የሚረጋገጥበትን ሁኔታ መፍጠር አለበት።
የዜግነት ፖለቲካ የሚከተለው ኢዜማ ፕሮግራሙ መሬት የሕዝብና የመንግስት እንዲሆን የሚፈቅድ ከመሆን ባለፈ ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ እንደሚሰራና የፌደራሊዝም ስርዓትን እንደሚከተል አስረድተዋል።
ኢዜማ ህገ መንግስቱ እንዲሻሻል አተኩሮ የሚሰራ፣ ፕሬዚዳንታዊ ስርዓትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በአገሪቱ እንዲሰፍን ማድረግና ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለማጥፋት አልሞ የተነሳ መሆኑን አስረድተዋል።
ስልጠናው በፓርቲው ፕሮግራምና እሴት ላይ የአመራሩንና የአባላቱን አቅም ለማጎልበ አልሞ እየተሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል።
በተጨማሪም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም፣ የዜግነት ፖለቲካ ምንነትና አተገባበር፣ የኢዜማ መርሆዎችና አሴቶች በሚሉ ርዕሶች ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።
የፓርቲው አባል የሆኑት አቶ ተስፋየ በየነ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት ሥልጠናው የፓርቲውን ፕሮግራም እሴት በመጨበጥ እስከታች ድረስ ለማሳወቅ ግንዛቤ ለማግኘት የሚያስችል ነው።
ባለፉት በርካታ ዓመታት ለተሰራው የጽንፈኝነት ፖለቲካና መፍትሄው የዜግነት ፖለቲካ መሆኑን የስልጠናው ተሳታፊዎች ግንዛቤ የሚያገኙበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አቶ ያረጋል ፈንታው የተባሉ ሌላው ተሳታፊ በበኩላቸው ሥልጠናው የኢዜማን ዓላማ በግልጽ ተገንዝበው ለአባላትና ለህብረተሰቡ ለማስረዳትና ለምርጫ ለመዘጋጀት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡