በምእራብ ሸዋ ዞን የ378 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ተጀመረ

58
አምቦ ሰኔ 15/2010 በምእራብ ሸዋ ዞን 22 ወረዳዎች የተዘጋጀ የ378 ሚሊዮን  ችግኝ ተከላ መጀመሩን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በጽህፈት ቤቱ የጥምር ደንና እርሻ ባለሙያ ወይዘሮ ፋንታዬ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለፁት ችግኙ የተዘጋጀው በዞኑ በሚገኝ ከ8 ሺህ በላይ በመንግስት፣ በግል፣ በማህበራት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ነው። በመተከል ላይ ካሉው ችግኝ መካከል 300 ሚሊዮኑ ባህር ዛፍን ጨምሮ ፅድ፣ ግራር፣ ዋንዛ፣ ኮሶና ሌሎች ለደን ልማት የሚውል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ቀሪው ደግሞ  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተሰራባቸው አካባቢዎች በስነ-ህይወታዊ ዘዴ ለማጠናከር የሚውልና ሁለገብ ጠቀሜታ ያላቸው የዕፅዋትና የእንሰሳት መኖ አይነቶች መሆናቸውን ገልፀዋል። “ችግኙ መሬት ላይ በተራቆተና ለምነቱ በተሟጠጠ በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል ድርሻው የጎላ ነው'' ብለዋል። ችግኙ በዞኑ በበጋ ወቅት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በተካሄደበት 32 ሺህ 657 ሄክታር መሬት ላይ ይተከላል፡፡ እስከ ሃምሌ ወር መጨረሻ ለሚቆየው የችግኝ ተከላ ከ149 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ይሆናሉ ። የአቡና ግንደበረት ወረዳ የጀሞ ፍኖ  ቀበሌ አርሶ አደር ዳኜ ዲርርሳ በሰጡት አሰተያየት በየዓመቱ በሚካሄደው የችግኝ ዝግጅትና ተከላ መሳተፋቸው በተለያየ ምክንያት ተመናምኖ የነበረው የደንና የግጦሽ መሬት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ለእንስሳት መኖ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። ከ500 በላይ የተለያየ የዛፍ ችግኝ ለመትከል አቅደው በአሁኑ ጊዜ ተከላ መጀመራቸውን የተናገሩት ደግሞ የአምቦ ወረዳ ቆራ ቀበሌ አርሶአደር ንጉሴ ፊጣ ናቸው፡፡ በሊበን ጃዊ ወረዳ የሮጌ ዳኒሳ  ቀበሌ አርሶ አደር አበበ ለታ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት የተከሉት የሳር ችግኝ  በዘንድሮ  የበጋ  ወራት የእንስሳት መኖ እጥረት እንዳቃለለላቸው ተናግረዋል፡፡ በዘንድሮው  ክረምት በችግኝ ዝግጅትና ተከላ  በራሣቸው ተነሳሽነት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት በዞኑ ከተተከለው 215 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ 65 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው መጽደቁንም  ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል ። በምዕራብ ሸዋ ዞን 104 ሺህ 799 ሄክታር የሚሸፍን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደን ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም