የዋቢ ሸበሌ ወንዝ መሙላቱን ተከትሎ ለተፈናቀሉ ወገኖች በአውሮፕላንና በሄሊኮፕተር የታገዘ እርዳታ እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዋቢ ሸበሌ ወንዝ መሙላቱን ተከትሎ ለተፈናቀሉ ወገኖች በአውሮፕላንና በሄሊኮፕተር የታገዘ እርዳታ እየተሰጠ ነው
ጅግጅጋ ግንቦት 2/2010 በሶማሌ ክልል የዋቢ ሸበሌ ወንዝ መሙላትን ተከትሎ ለተፈናቀሉ ወገኖች በአውሮፕላንና ሄሊኮፕተር አስቸኳይ እርዳታ ማድረስ መጀመሩን የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ አስታወቀ፡፡ ቢሮው የችግሩን አጣዳፊነት ግምት ውስጥ በማስገባትና የመኪና መንገድ በመበላሸቱ ምክንያት ከፌዴራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ካለፈው እሁድ ጀምሮ አውሮፕላንና ሄሊኮፕተር በመጠቀም ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡ በቢሮው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አብዲ አህመድ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ከሦስት ሳምንት በፊት በሙስታሂል እና ቀላፎ ተከስቶ በነበረው የወንዝ ሙላት ምክንያት ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል። በእዚህም ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስቸኳይ እርዳታ ለማቅረብ ጥረት ቢደረግም ከጎዴ ከተማ እስከ ሙስታሂልና ፌርፌር ያለው ጥርጊያ መንገድ በውሃ መሙላት ምክንያት ከጥቅም ውጪ በመሆኑ አርዳታውን በተሸከርካሪ ለማጓጓዝ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል። እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ለአንድ ሳምንት በጎዴ ከተማ ከቆሙ በኋላ የክልሉና የፌዴራል መንግስት በጋራ በመነጋገር አስቸኳይ መፍትሄ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በእዚህም በሁለት የጭነት አውሮፕላኖች እርዳታውን ከቢሾፍቱ እስከጎዴ አየር ማረፊያ ድረስ ጭነው የሚያመጡ ሲሆን ሦስት ሄሌኮፕተሮችም ከጎዴ አየር ማረፊያ ተጎጂዎች ወደሚገኙበት አካባቢ በማድረስ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ እስካሁንም ለተጎጂዎች አልሚ ምግቦች፣ ሩዝ እና ሌሎች የቤት ውስጥ መገልገያና የሕክምና ቁሳቁሶችን ማድረስ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡ የተፈናቃይ ወገኖችን ችግር ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መንግስት የአየር ማጓጓዣን እንደአማራጭ መጠቀሙ በእርዳታ አቅርቦቱ አጋጥሞ የነበረውን መስተጓጎል በተወሰነ ደረጃ እንዳቃለለው አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ በእዚህ ሁኔታ የህክምናና የምግብ እርዳታ በተቀላጠፈ መንገድ ለማቅረብም ሆነ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ብዙ ወጪ ስለሚጠይቅ የተዘጉ የተሽከርካሪ መንገዶች ወደሥራ የሚገቡበት መንገድ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል። የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ ዩሱፍ ኢስማን በበኩላቸው በታችኛው የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ወንዞችና ተፋሰሶች ላለፉት አስር ዓመታት ባልታየ መልኩ ሞልተው በመፍሰስ ከወንዙ ራቅ ያሉት መንደሮችን ማጥለቅለቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ወር በክልሉ በተለያዩ ወቅቶች በጣለው ዝናብ እና ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ፣ ባሌና አርሲ የሚፈሱ ወንዞች በመሙላታቸው በፋፈን፣ ሲቲ፣ ሸበሌ፣ ሊበንና አፍዴር ዞኖች ከ163 ሺህ በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች ላይ ጎዳት መድረሱ ይታወሳል። ዋቢ ሸበሌ ወንዝ ሞልቶ ሲፈስ በየጊዜው በነዋሪዎች ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ የገለጹት አቶ ዩሱፍ አደጋው ሲደርስ የእለት እርዳታ ማቅረብ ብቻ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይሆን ገልጸዋል። " በጥናት ላይ የተመሰረተ የጎርፍ መከላከል ሥራዎችን አስቀድሞ ለማከናወን በቢሮ ደረጃ በየዓመቱ ቢታቀድም በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ሊሳካ አልቻለም " ብለዋል፡፡ ወንዙ በነዋሪዎች ላይ የሚፈጥረውን ጉዳትና የሚያስከትለውን የመሰረተ ልማት ውድመት በዘላቂነት ለማስቀረት የሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል አካላት ለጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ቡድን መሪው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የክልሉ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ሥራ ኢስከያጅ ኢንጂነር አሰድ ኡመር በበኩላቸው ስለጉዳዮ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ከጎዴ እስከ ፌርፌር ከተማ ያለው 290 ኪሎ ሜትር ነባር ጥርጊያ መንገድ በአገልግሎት ብዛትና በጎርፍ ምክንያት ከጥቅም ውጪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "መንገዱ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳ በመሆኑ በውሃ ምክንያት የፈረሱ ድልድዮችንና የተንሸራተቱ ቦታዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያስፈልገው ወጪ ከክልሉ አቅም በላይ ሆኗል" ብለዋል፡፡ የወንዝ ሙላቱ በድንገት የተከሰተ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ዕቅድ አለመያዙን የገለጹት ሥራ አስከያጁ፣ የችግሩን ስፋትና ከአቅም በላይ መሆኑን ከሁለት ሳምንት በፊት ለፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን በማሳወቅ የድጋፍ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደሥራ አስኪያጁ ገለጻ በሊበን፣ አፍዴርና ሸበሌ ዞኖች የሚገኙ ዋቢ ሸበሌና ገናሌ ወንዞች እንዲሁም ተፋሰሶች በዝናቡ ምክንያት በመሙላታቸው መንገዶችና አስር ድልድዮች በጎርፍ ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል፡፡ ጎዴ፣ ቀላፎ፣ ሙስታሂልና ፌርፌርን የሚያገናኘው መንገድ ድንበር ተሻጋሪ መንገድ በመሆኑ የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን ከሚያስተዳድራቸው መንገዶች ውስጥ የሚመደብ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን የኮሙዩኔክሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በሶማሌ ክልል ታችኛው አከባቢ ለብልሽት ከተዳረጉ መንገዶች መካከል ከጎዴ ሀርጌሌ እና ኢሜ ከተሞች የሚያገናኘው መንገድ ከባድ ብልሽት እንደገጠመው ገልጸዋል። በቅርቡ የጥገና ባለሙያዎችን ወደስፍራው ለመላክና ፈጣን ጥገና ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት አቶ ሳምሶን ከጎዴ፣ ቀላፎ፣ ሙስታሂልና ፌርፌር ድረስ ያለው መንገድ ግን የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።