የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል የአብሮነታችን በዓል ነው… ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል የአብሮነታችን በዓል ነው… ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
እንኳን የኢትዮጵያዊነት ቀን ለሆነው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አደረሳችሁ፡፡ ይህ በዓል የአብሮነታችን በዓል ነው፡፡ ምን ያህል ልዩ፣ ክቡር፣ ውድ፣ አስደናቂ፣ ኅብረ ብሔራዊ ባህሎችና ማንነቶች እንዳሉን የምናሳይበት በዓል ነው፡፡ ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተዛመዱ፣ የተጋመዱ፣ የተወራረሱ፣የተሠናሠሉ፣ መሆናቸውንም የምናይበት በዓል ነው፡፡ እንዲሁ ተሰባስበን አንድ ቦታ ላይ የተከማቸን አይደለንም፡፡ አብረን ኖረናል፡፡ አብረን በኖርንባቸው ዘመናት ብዙ ነገሮችን ተወራርሰናል፡፡ ስኬቶቻችንንና ድሎቻችንን ብቻ ሳይሆን መከራዎቻችንንና ግፎቻችንን ተካፍለናል፡፡ ባህሎችንና ዕሴቶችን አንዳችን ከሌላችን ወርሰናል፤ ተጋብተን ተዋልደን በደም ተሣሥረናል፡፡ አንድ ቦታ መኖር ብቻ ሳይሆን ለአንድ ዓላማ በአንድ ግንባር ተሠዉተናል፤ በአንድ መቃብር ተቀብረናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ለእኩልነት፣ ለነጻነትና ለፍትሐዊነት ታግለዋል፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ባህልንና ቋንቋን የማበልጸግ መብት ለማግኘት መሥዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሁሉም እኩል መሥዋዕትነት ሲከፍሉባት የኖረች ሀገራቸው በመሆኗ ሁሉም እኩል የሚጠቀሙባት ሀገር እንድትሆን ከገዥዎች ጋር ተናንቀዋል፡፡ ይህ የዘመናት ትግላቸው በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና አግኝቶ ራስን የማስተዳደር መብታቸው ተረጋግጧል፡፡ በተግባር ሲፈተሽ ግን የዘረጋነው ሥርዓት ትግላቸውን በተሟላ ሁኔታ የሚመልስ፣ መብታቸውንም በእኩልነት የሚያስከብር አልነበረም፡፡ አሐዳዊነት በፌዴራላዊነት ሳይሆን በእጅ አዙር አሐዳዊነት ተተካ፡፡ ብሔረሰቦችን ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር እንዲችሉ የተመሠረቱት አብዛኞቹ ክልሎች በጡት አባቶች እንዲተዳደሩ ተደረጉ፡፡ ክልሎች በተፈጥሮና ሰው በሠራሽ ሀብቶቻቸው የበዪ ተመልካቾች ሆኑ፡፡ ሀገር ለመምራት የሚፈቀድላቸውና የማይፈቀድላቸው ብሔረሰቦች ተፈጠሩ፡፡ የተወሰኑት ከበሮውን ሲመቱ ሌሎች አጋሮች ሆነው እንዲያጨበጭቡ ብቻ ተፈቀደላቸው፡፡ በሕዝብ መራራ ትግል የሕዝቡን ሉዓላዊነትና መብት ለማስከበር የወጣው ሕገ መንግሥት እየተሻረ የጥቂቶች አገዛዝ መስፈን ጀመረ፡፡ ሰብአዊ መብቶች ተጣሱ፣ የዜጎች ክብር ጠፍቶ ኢትዮጵያ የጨለማ እሥር ቤቶችና የማሰቃያ ሥፍራዎች መናኸሪያ ሆነች፡፡ የክልሎች መሬት ያለ እነርሱ ፈቃድ ለእጅ አዙር አሐዳውያን ተሸነሸነ፡፡ ሀብታቸውና ንብረታቸው ተመዘበረ፤ በየክልሉ የተዘረጉት ታላላቅ ፕሮጀክቶች የእጅ አዙር አሐዳውያን የምዝበራ ማዕከላት ሆኑ፡፡ ለምን? ብለው የጠየቁ ሁሉ ከአራዊት ጋር ታሠሩ፤ ተኮላሹ፤ እግርና እጃቸው ተቆረጠ፤ ከሀገር ተሰደዱ፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች ወደ ዳግም ትግል የከተታቸው፡፡ ከለውጡ በፊት ወደነበረው ማዕበል የወሰዳቸው፡፡ የእጅ አዙር አሐዳዊነትን አንፈልግም ብለው ለመብቶቻቸውና ለነጻነታቸው እንዲዋደቁ ያደረጋቸው፡፡ ትክክለኛውን ፌዴራላዊ ሥርዓት ለማምጣት ሲሉ፣ አንድ ሆነው፣ የእጅ አዙር አሐዳውያንን ለመጣል የተነሡት፡፡ ሕገ መንግሥቱ በልኩና በመጠኑ ያህል እንዲተገበር ሲሉ የሕይወት መሥዋዕትነት የከፈሉት፡፡ ዛሬ ያለንበት ጊዜ ለብሔረሰቦች ትግል መልስ በመስጠት ላይ ያለንበት ጊዜ ነው፡፡ የእጅ አዙር አሐዳዊነት ቀርቷል፡፡ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ክልል የሚባለው አሠራር ጠፍቷል፡፡ የበዪና የተመልካች አሠራር ተወግዷል፡፡ ዋናና ተባባሪ የሚባለው ክፍፍል ላይመለስአክትሟል፡፡ አንድ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል የሚመጣ ኢትዮጵያዊ የመጨረሻውን የኢትዮጵያ ሥልጣን ሊይዝበት የሚችለው ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ክልሎች በሞግዚቶች ሳይሆን በራሳቸው የሚተዳደሩበት እውነተኛው ፌዴራሊዝም መሬት ላይ ወርዷል፡፡ የታላቋን ሀገራቸውን የኢትዮጵያን ሀብት፣ ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅነት እንዳያልሙ ሲባል ብሔረሰቦች ስለ ልዩነታቸው እንጂ ስለ ኢትዮጵያዊ አንድነታቸው እንዳያስቡ ተደርጓል፡፡ ሀገራዊ አንድነት ከብሔር ማንነት ጋር ሆን ተብሎ እንዲጣላ ተሠርቷል፡፡ አንዳንዶች ከጠቅላላዋ ኢትዮጵያ እንዲጠቀሙ፤ብዙዎች ግን ከአካባቢያቸው ብቻ እንዲጠቀሙ ሲሠራ ኖሯል፡፡ ያ ጊዜ አሁን አብቅቷል፡፡ እኛኅብራውያን ነን፡፡ ኅብር ስንል በአንድ በኩል እንደ ኅብረ ቀለማት የየራሳችን ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ያለን ነን፡፡ በሌላ በክል ደግሞ ‹ኅብር› ስንል አብረን፣ ተባብረን የኖርን፣ ኢትዮጵያ የምትባለውን ቤት በጋራ የገነባን፤ አብረን ድል ያደረግን፣ አብረን የተጨቆንን፣ አብረን ብሔራዊ ገዥዎችን የታገልን፣ አብረን ቅኝ ገዥዎችን ያንበረከክን ነን፡፡ ይህን በዓል ስናከብር ወደ ቀደመው አሐዳዊነትም ሆነ ወደ እጅ አዙር አሐዳዊነት ዳግም እንደማንመለስ እያረጋገጥን ነው፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓታችን ስሙን ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ አተገባበሩን በትግላችን እንደጨበጥነው እያረጋገጥን ነው፡፡ ተጨዋችና ተመልካች ክልሎች ከዚህ በኋላ እንደማይኖሩ እያረጋገጥን ነው፡፡ ኅብረ ሀገራዊ አንድነታችንን መቼም ቢሆን ለድርድር እንደማናቀርበው እያረጋገጥን ነው፡፡ አንድነታችን ልዩነታችንን ሳይጠቀልለው፤ ልዩነታችንም አንድነታችንን ሳይሸረሽረው አብርን ልንኖር ዳግም ቃል የምንገባበት በዓላችን ነው፡፡ ስለ ድህነት መቆዘማችንን አቁመን ስለ ብልጽግና ለመዘመር፣ ስለ መነጣጠል መስማታችንን ትተን ስለ መደመር አብረን ለመቆም መወሰናችንን የምናረጋግጥበት በዓላችን ነው፡፡ ከፊታችን ያለው ዘመን መንፈሳዊ፣ አእምሯዊና ቁሳዊ ብልጽግናችን የሚረጋገጥበት ዘመን ይሆናል፡፡ ባህሎቻችን፣ ቋንቋዎቻችን፣ ዕሴቶቻችን፣ የሚበለጽጉበት ዘመን ይሆናል፡፡ አንድነታችን፣ አብሮነታችን፣ ወንድማማችነታችን የሚበለጽግበት ዘመን ይሆናል፤ በዕውቀትና በሀብት የምንበለጽግበት ዘመን ይሆናል፡፡ በፍትሕ፣ በሰላም፣ በጋራ ደኅንነት፣ የምንበለጽግበት ዘመን ይሆናል፡፡ ካሳለፍናቸው ዘመናት ይልቅ ወደፊት የምናሳልፋቸው ዘመናት ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም በቀደመው ዘመንና አስተሳሰብ ላይ ተቸክለን አንቀርም፤ በወደፊቱ ጎዟችን ላይ አተኩረን የብልጽግናን ጎዳና አጽንተን እንይዛለን፡፡ በድጋሚ የኢትዮጵያዊነት ቀን ለሆነው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እንኳን አደረሳችሁ፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ! ህዳር 28 ቀን 2012 ዓ.ም