ቀጥታ፡

የብልፅግና ፓርቲ ሪፎርም መነሻው የህዝቡን ፍላጎትና ጥቅም ማስጠበቅ ነው--- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

ኢዜአ ህዳር 27/2012 የብልፅግና ፓርቲ ሪፎርም መነሻው የህዝቡን ፍላጎት ለማሳከትና ጥቅሙን ለማስጠበቅ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ። የኦዲፒ  ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በፓርቲው ህገ ደንብ፣ ፕሮግራምና ዓላማ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ አባገዳ አደራሽ ተጀምሯል። አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመድረኩ እንደገለጹት የፓርቲው ፕሮግራምና ዓላማ የህዝቡን የመልማት፣የመብትና እኩል ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ የተቃኘ ነው። የኦሮሞንም ሆነ የሌሎችንም ህዝቦች ፍላጎቶችንና ጥቅሞችን መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎችን መመለስ በግንባሩ አካሄድ እንደማይቻል አመልክተዋል። ባለፉት 27 ዓመታት ህገ መንግስቱን በተንፃረረ መልኩ የብዙሃን ድምፅ የጨፈለቀና የጥቂቶች የበላይነት ያረጋገጠ አካሄድ እንደነበር ተናግረዋል። አቶ ሽመልስ እንዳሉት የፓርቲው ውህደትና ሪፎርም ያስፈለገው የህዝቡን ፍላጎት ለማሳከትና ጥቅሙን ለማስጠበቅ ነው። "የብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራምና ዓላማ ህብረብሔራዊ የፌዴራልዝም ሥርዓት በትክክለኛ ፅኑ መሰረት ላይ እንዲገነባና ዴሞክራሲ በሀገሪቱ እንዲያብብ  ለማስቻል እንጂ መቼም ቢሆን ወደኋላ የሚመለስ አይደለም "ብለዋል። ባለፉት 27 ዓመታት ብቻ የክልሎች ሉዓላዊና ህገ መንግስታዊ የስልጣን ባለቤትነት የሚጥሱና የሚንፃረሩ 29 አዋጆች በፌዴራል መንግስት ተደንግገው ሥራ ላይ መዋላቸውን ጠቅሰዋል። አዲሱ ፓርቲ ክልሎች የራሳቸውን ዕድል በራስ የመወሰንና የማስተዳደር ትክክለኛ ፌዴራልዝም እንዲተገብሩ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል። እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ የብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነት፣ባህልና ቋንቋ ይበልጥ የሚበለፅግበት ፕሮግራምና ዓላማ በግልፅ ያስቀመጠ ነው። የህዝቡን የፖለቲካ፣ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ቆሞ የቀረውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ በማስወገድ ወቅቱ የሚፈለገውን ሃሳብ ማመንጨትና ማራመድ የሚችል አዲስ ፓርቲ መመስረት ማስፈለጉን አስረድተዋል። የመድረኩ ዓላማ በፓርቲው ህገ ደንብ፣ፕሮግራሞች ፣ዓላማዎችናበአጠቃላይ ሪፎርሙ ዙሪያ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በቂ ዕውቀት፣ክህሎትና ግልፅ ግንዛቤ እንዲኖረቸው ለማስቻል መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ናቸው። በቀጣይም እስከ ዞኖች ወረዳዎች፣ ከተሞችና ቀበሌዎች ድረስ በመውረድ ለመሰረታዊ አባላት በፓርቲው ፕሮግራሞች፣ዓላማዎችና አጠቃላይ ሪፎርሙ ዙሪያ ስልጠና እንደሚሰጥ አስታውቀዋል። "ውህደቱ ያስፈለገበት ዋና ዓላማ ትክክለኛ ፌዴራልዝም በመገንባት አሳታፊና አቃፊ የሆነ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ነው" ያሉት አቶ ፍቃዱ ይህም አሁን ግንባሩ ባለበት ሁኔታና በቀድሞ ፕሮግራሞቹ ሀገሪቱን ማስቀጠል ባለመቻሉ እንደሆነ አመልክተዋል። በዚህም አዲስ የሚመሰረተው ፓርቲ የህዝቦችን ሁሉን አቀፍ ጥያቄ ከመሰረቱ ለመመለስ የሚያስችለውን አደረጃጀትና ቁመና እንዲኖረው ለማስቻል ነው ተብሏል። ለአራት ቀናት በሚቆየው መድረክ ከኦሮሚያ 20 ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከ2ሺህ በላይ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም